ይህ የአማራ ትሥሥርር በቻይና ይፋዊ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ድረ-ገጽ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ልማድ፣ አርበኝነት፣ ቅርስ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችንም ጭምር ለአባላት በሚገባ እናሳውቃለን። የድረ-ገጹ ዋና አላማ የአማራን ታሪክ በሚገባ ለሁሉም በማስተማር ታሪካችንን ወደቀደመ ልዕልናው መመለስ ነው። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤ አንዲት ነጻ ሃገር ኢትዮጵያ -->

Shewareged Gedle

 የታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ 73ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ


የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በአርበኝነት ተጋድሎ ዘመን የማይሽረው አኩሪ ገድል ከፈፀሙት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ የነበሩት ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ያረፉት ከዛሬ 73 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 22 ቀን 1942 ዓ.ም) ነበር። አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ የተወለዱት በ1878 ዓ.ም ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ ነው። የቤተ-ክህነት ትምህርት ተምረዋል። ለአቅመ ሔዋን ሲደርሱ ያገቧቸው ባል ብዙም ሳይቆዩ ስለሞቱባቸው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገብተው ተቀምጠው ቆይተዋል። 

በ1888 ዓ.ም በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ድል የሆነው የኢጣሊያ ጦር ቂሙን ሳይረሳ ሽንፈቱን ሳይዘነጋ ከአርባ አመታት በኋላ ዳግመኛ ለብቀላ በተመለሰበት አጋጣሚ በአዲስ አበባ ከተማ በአገር ተቆርቋሪ ዜጎች መስራችነት የሀገር ፍቅር ማኅበር ተቋቋመ። በማኅበሩ በአባልነት ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመዘገቡ ሴቶች መካከልም ጀግናዋ ሸዋረገድ ገድሌ አንዷና ግንባር ቀደም ነበሩ። ወራሪው የኢጣሊያ ጦር አገራችን እንደገባ የመጀመሪያ ተግባሩ ያደረገው ለዘመናት በድል ሲውለበለብ የቆየውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በማውረድ የራሱን ባንዲራ መተካትን ነበር። በወቅቱ ይህን ድርጊት በአይናቸው የተመለከቱት ሸዋረገድ ግን ወራሪውን ጦር ሳይፈሩና ሳይሳቀቁ አገሬ ተወረረች፤ ተዋረደችም ሲሉ አምርረውና ጮኸው ማልቀሳቸውን ተያያዙት። 

ሁኔታቸውን ያዩ የጣሊያን ሹማምንትም የእርሳቸውን ድርጊት እንደ ድፍረት በመቁጠር ለክስ አቀረቧቸው። ሸዋረገድ ግን በተለየ ወኔ ተሞልተው አዎ አልቅሻለሁ! የአገሬን መወረርና መዋረድ ያወቅሁት የኛ ሰንደቅ አላማ ወርዶ የእናንተ ሲወለበለብ በማየቴ ነው። ሰው ለእናት አገሩ ቢያለቅስ ነውሩ የቱ ላይ ነው?! ሲሉ እልህ በተሞላበት ሁኔታ መለሱላቸው። 

ሸዋረገድ አገራቸው በጠላት ጦር ዳግመኛ መወረሯ ከታወቀ ወዲህ ሕይወቴ ሀገሬ ናት ሲሉ ለመታገል ቆረጡ። ከወራሪው የጠላት ጦር ጋር ሊፋለምና ደሙን ለሀገሩ ሊገብር ለተዘጋጀው ወገን ያላቸውን ሁሉ ሸጠው ትጥቅ እያደራጁና ስንቅ እያዘጋጁ እንዲሁም ከኢትዮጵያውያን ሴቶችም ቁርጥራጭ ጨርቆችን እያሰባስቡ በጦርነቱ ለሚጎዱ ቁስለኞች እንዲላክ ያደርጉና ይሰጡ ጀመር። የእሳቸው ድርጊት ግን ለጣሊያኖቹ ሰላም አልሰጠም። ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት አልፈው ለክስ እንዲቀርቡ ወሰኑባቸው። ወይዘሮ ሸዋረገድ ለአርበኞች ስንቅ በማቀበላቸው፣ መሣሪያ በመግዛታቸው፣ መረጃ በማሰባሰባቸው፣ መድኃኒት በመላካቸውና ሞራል በመስጠታቸው ምክንያት በተከሰሱ ጊዜም ለአርበኞች ስንቅ ማቀበሌ እውነት ነው፤ ይህንንም ያደረግኩት ለሀገሬ ክብር ብዬ ነው። ሰው እንኳን ለሀገሩ … የእናንተ ወይዛዝርት ሀገራቸው ያልሆነቺው ኢትዮጵያን ለመውረር የጣታቸውን ቀለበት ሳይቀር መስጠታቸውን ትናገራላችሁ። እኔም ለሀገሬ የሠራሁት ሲያንሰኝ እንጂ አይበዛብኝም! በማለት ስለፈፀሙት ድርጊት ሁሉ ኩራት እንደሚሰማቸውና ይህንንም ያደረጉት ለአገራቸው ክብር ሲሉ እንደሆነ በድፍረት ተናገሩ።

ወይዘሮ ሸዋረገድ ከሚጠቀሱላቸው ሥራዎቻቸው አንዱ ለቀይ መስቀል ማኅበር ያደርጉት የነበረው ድጋፍ ነው። በጦርነቱ ዋዜማ፣ በ1927 ዓም ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ንብረታቸውን ሸጠው በማስረከብ አገር ወዳድነታቸውን አስከብረዋል። ከተከሰሱባቸውና ወንጀል ተደርገው ከተቆጠሩባቸው ድርጊቶች መካከል አንዱ ይኸው ለቀይ መስቀል ያደርጉት የነበረው ድጋፍ ነው።  እሥር ቤት በገቡ ጊዜም የፋሺስት አስተዳደር ባለስልጣናት ቀይ መስቀልንና ሀገር ፍቅር ማኅበርን ትረጃለሺ ብለው ክስ አቅርበውባቸው ነበር። የጠላቶቻቸውን ክስ ከቁብ ያልቆጠሩት አርበኛ ሸዋረገድ ግን ስለ ነፃነት ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው የሌሊት ቁርና የቀን ሐሩር ከሚገርፋቸው የአገሬ አርበኞች ጎን ተሰልፌ ጠላቴን መውጋቴ ቀርቶ የረሀብና የጥም መድኃኒት እያዘጋጀሁ መላኬ ቁም ነገር ሆኖ ነው የተጠየቅሁበት? እኔ ይህን ባለማድረጌና ለሀገርም ባልቆረቆር፤ እንኳን እነሱ እናንተም እንደምትታዘቡኝ ይሰማኛል በማለት እጅግ አስደናቂ የሆነ የሀገር ፍቅር የተሞላበትና ቆራጥነት የተቀላቀለበት መልስ ሰጥተዋል።

አርበኛ ሸዋረገድ ከቁሳቁስ እርዳታው ጎን ለጎን ለአርበኞቹ የመረጃ ምንጭም ነበሩ። በከተማው የሚገኙ የጠላት መረጃዎችን በማሰባሰብና ወደ አርበኞች በምሥጢር በመላክ አርበኞች እንዲጠቀሙባቸው አድርገዋል። ይህ ተግባራቸውም ከወቅቱ የውስጥ አርበኞች መካከል አንዷና ዋነኛዋ ሆነው እንዲቆጠሩ አስችሏቸዋል። ሸዋረገድ ለኢጣሊያ ሰዎች ወዳጅ በመምሰል ለኢትዮጵያውያን አርበኞች መረጃ ይሰጡ ስለነበር የኢጣሊያ ፋሺስቶች ሸዋረገድ እውነተኛ ወዳጃቸው መስለዋቸው አርበኞችን ከረዳሽ እኛን አትወጂንም ማለት ነው? ብለው ሲጠይቋቸው አዎ አልወዳችሁም! ማነው የአገሩን ደመኛ የሚወደው? በማለት ቁርጥ ያለ ምላሽ ሰጥተዋቸዋል።

        

አርበኛዋ ሸዋረገድ በሚፈፅሟቸው በርካታ ፀረ-ፋሺስት እንቅስቃሴዎች ምክንያት ጥርስ የነከሱባቸው የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደር ባለስልጣናት ሕይወታቸውን በእስር እንዲገፉና ቆይቶም ሞት እንዲፈረድባቸው ወስነው ነበር። ሆኖም አዚናራ ወደምትባልና በሰሜናዊ ምዕራብ ኢጣሊያ ወደምትገኝ ደሴት ታስረው እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ፍርዱ ወደ እስራት ብቻ በመቀየሩ ምክንያት የእስር ዘመናቸውን በደሴቲቱ እንዲገፉ ተወሰነባቸው።

ጀግናዋ አርበኛ ሸዋረገድ ግን የቦታ ለውጥና ርቀት አልበገራቸውም። በጠላት አገር ሆነውም ጽናታቸው አልተሰበረም፤ ወኔያቸውም አልተሰለበም። እንዲያውም ወኔያቸውን አጠናክረው ትግላቸውን ቀጠሉ። በእስር ቤቱ የሚቀርብላቸውን ምግብ በአሳሪዎቻቸው ፊት በመድፋትና ጦማቸውን ውለው በማደርም ተቃውሞ ማድረግ ጀመሩ። ከአንድ ዓመት የእስራት ቆይጣ በኋላ ከእስራት እንዲለቀቁ በመወሰኑም ወደ አዲስ አበባ የመግባት እድል አገኙ። በወቅቱ ወደ አዲስ አበባ ሲገቡም ሕዝቡ … 

የዘበኛ ሱሪ ካኪና ገምባሌ፣

እንኳን ደህና መጣሽ ሸዋረገድ ገድሌ።

 ብሎ በመግጠም ተቀበላቸው።

በተለይ በጅቡቲ የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ የሰጣቸውን የይሁዳ አንበሳ የሚል ጽሑፍና ዓርማ ያለበትን ወረቀት ከንጉሠ ነገሥቱ የተላከ የሚመስል መልዕክት እየፃፉ አርበኞች ተጋድሎ ወደሚደርጉባቸው ልዩ ልዩ ስፍራዎች በመላክ አርበኞቹ እንዲበረታቱ አድርገውበታል።

አዲስ ዓለም አካባቢ ይገኝ የነበረው የፋሺስት አጣሊያ ምሽግ ኅዳር 5 ቀን1933 ዓ.ም ሲሰበር ጠቃሚ መረጃዎችን ለአርበኞች በማሰባሰብና በርካታ እቅዶችን በመንደፍ ታላቁን ድርሻ የተወጡት ታላቋ አርበኛ ሸዋረገድ ነበሩ። ምሽጉ ከተሰበረም በኋላ ደጀን መሆኑን ትተው ወደ ውጊያ ለመግባት በመወሰናቸው ከሻለቃ በቀለ ወያ ጦር ጋር ተሰልፈው ጠላትን ተፋልመዋል። በመቀጠልም ወደ ወሊሶ በመሄድ ከደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጦር ጋር ሆነው ተዋግተዋል። በጦርነቱ የአራት ሰዓታት ውጊያ ላይ ጠላት በጣለው ድንገተኛ አደጋ ከታላቅ ተጋድሎ በኋላ የተማረኩት አርበኛ ሸዋረገድ፣  በድጋሜ በፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች እጅ በመውደቃቸው የፊጥኝ ታስረው ወደ እስር ቤት ተወረወሩ። 

የሸዋረገድን ጀግንነት የተመለከተው ሕዝብም …  

የምታስፎክር ሰንጋ ገለሌ፣

በጦር መካከል ሳይሆኑ አያሌ፣

በጥይት ገዳይ ነጭ ብር ገድሌ፣

የሴት ወንድ ናት ሸዋረገድ ገድሌ። ብሎ ጀግንነታቸውን በማድነቅ አወድሷቸዋል፡፡ 

የጀግኖች አርበኞች ትግል ተጠናክሮ የጠላት ጦር በመጣበት እግሩ በታላቅ ውርደትና በአሳፋሪ ሽንፈት በ1933 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ሲባረር ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌም ነፃ ሆነው ተፈቱ። ከዚህ በኋላ ሕይወትን በነፃነት ማጣጣም ለእኚህ ታላቅ ሴት ትልቅ ትርጉም ነበረው። ቀድሞ የጀመሩትን አርበኞችን የመርዳት የበጎ አድራጎት ስራቸውን አጠናክረው ቀጠሉበት። በንግዱ ዘርፍ ተሰማርተውም በርካታ ሰዎችን እንደጠቀሙም ይነገርላቸዋል።  

ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ታዋቂ ያደረጋቸው የአርበኝነት ስራቸው ሆነ እንጂ ከመጀመሪያዎቹ የባንክ ተጠቃሚዎች፣ የአክሲዮን ገዥዎች፣ የፋብሪካ ተካዮች መካከል አንዷ ነበሩ። በነዚህ የንግድ ስራዎቻቸውም በርካታ ሰዎችን በተለይ ደግሞ ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻሉ ታሪካቸው ያስረዳል። በሃይማኖታቸውም ጠንካራ እንደነበሩ ታሪካቸው የሚናገረው አርበኛዋ፣ የጉለሌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያንንም ያስተከሉት እርሳቸው ናቸው። 

ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ለወቅቱ አርበኞች በመሳሪያ፣ በስንቅና በመረጃ ያደርጉላቸው ከነበረው ድጋፍ በተጨማሪ ከአንዳንዶቹ ጋር በጦር ሜዳ አብረው ተሰልፈው ተዋግተዋል። ለአብነት ያህልም ከጀግኖቹ አርበኞች ደጃዝማች በቀለ ወያ እና ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጋር ተሰልፈው ከጠላት ጦር ጋር ተፋልመዋል። ለታዋቂው አርበኛ ሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎም ልዩ አክብሮት ነበራቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ሊጠቀስ የሚገባው አንድ አጋጣሚ አለ። ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ተመልሠው ዙፋናቸው ላይ ቢቀመጡም ጎንደርና ጅማ ከጠላት ጦር አልተለቀቁም ነበር። መጀመሪያ የቅርቡን እናስለቅቅ ተብሎ ወደ ጅማ ሲሄዱ የፋሺስት ጦር የጊቤን ድልድይ ቆርጦ መከላከል ጀመረ። በዚህ ጊዜ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጃገማን ያውቋቸው ነበርና ለንጉሠ ነገሥቱ ለጃገማ ትዕዛዝ ቢሰጡልኝ በአምቦ መንገድ ሄዶ በኋላ በኩል ይቆርጥልኛል በማለታቸው ጃገማ ከደጃዝማችች ገረሱ ጋር እንዲዘምቱ በደብዳቤ ታዘዙ። 

አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ ለንጉሠ ነገሥቱ ጃንሆይ ይህ ልጅ ገና ሕፃንና የሚያምር ልጅ ነው፤ እንዴት ከሞት ወደ ሞት ይልኩታል? ጦሩን ቢያዩለትም መልካም ነው ብለው ስለተናገሩ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጦርህን መጥተን እናያለን፤ ተዘጋጅተህ ጠብቅ፤ፉከራም ታሰማለህ ብለው አዘዙ። ንጉሠ ነገሥቱም የጀግናውን ጦር ጎብኝተው ከጃገማ ጋር ምሳ በሉ። ከዚያም ጃገማ አዲስ አበባ መጥተው ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሽልማት (25ሺ ብር፣ የወርቅ ሰዓት እና ሙሉ ገበርዲን ሱፍ) ተቀበሉ። ከዚያም ጃገማ ወደ ደጃዝማች ገረሱ ዘንድ ዘምተውና የለመዱትን ጀብድ ፈፅመው በቦታው የነበረውን የፋሺስት ጦር ዋና አዛዥና ሌሎች መኮንኖችን ማርከው ጦርነቱንም በድል ፈጸሙ።

በመጨረሻም አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ ግሼን ማርያም ሄደው ሥጋ ወደሙን ተቀብለው፤ ከዚያም ወደ ላሊበላ ተጉዘውና ተሳልመው፤ የመጨረሻቸው መሆኑን እየተናገሩ ጥቅምት 22 ቀን 1942 ዓም ዐረፉ።  የታላቋና አይረሴዋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ የመሞታቸው ዜና እንደተሰማ ህዝቡ እንዲህ ብሎ አንጎራጉሮላቸው ነበር። 

እናንት ወጥ ቤቶች በርበሬ ቀንጥሱ፣

እናንት ስጋ ቤቶች ሰንጋውን ምረጡ፣

ሸዋረገድ ገድሌ ለገና ሲመጡ፡፡

ቤተሰቧ ሰፊ ገናና ጥምቀት፣

ሸዋረገድ ገድሌ እንደምን ትሙት፡፡

ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ በሕይወት ዘመናቸው ያሳዩት ከአለት የበረታ ጽናት፤ ከእቶን የጋለ አርበኝነት በአጠቃላይ የፈፀሟቸው ገድሎች ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ እንድትቆይ ከማስቻል አልፈው  ለአሁኑ ዘመን ኢትዮጵያውያን (በተለይም ለወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች) በአርዓያነት የሚጠቀሱ ድንቅ ተግባራት ናቸው። ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ የአብራካቸው ክፋይ የሆነ ልጅ አላፈሩም። የልጅ መካን ቢሆኑም የአኩሪ ታሪክ እናት በመሆናቸው ስማቸው በጀግንነት ሕያው ሆኖ ይኖራል።

አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል


የአማራ ትስስር በቻይና

ጥቅምት 22  2015 ዓ.ም 

ቻይና

የአማራ ትስስር በቻይና(ANiC)

የአማራ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ፣ ሃይማኖትና ባህል ያለው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት የሆነ፤ ሃገር የሰራ፣ ነጻነቱን ያስጠበቀ፤ የራሱ የሆነ ፊደል ያለው፤ የጥንታዊ ትምህርት ስርዓት ባለቤት የሆነ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ በሃገረ መንግስት ምስረታ ሃገርን ከወራሪ መጠበቅና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ታላቅ ገድል በመስራት እኛ ልጆቹ ቀና ብለን እንድንሄድ አድርጎናል።

Post a Comment

ቀዳሚ ገጽ ተከታይ ገጽ
hi