ይህ የአማራ ትሥሥርር በቻይና ይፋዊ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ድረ-ገጽ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ልማድ፣ አርበኝነት፣ ቅርስ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችንም ጭምር ለአባላት በሚገባ እናሳውቃለን። የድረ-ገጹ ዋና አላማ የአማራን ታሪክ በሚገባ ለሁሉም በማስተማር ታሪካችንን ወደቀደመ ልዕልናው መመለስ ነው። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤ አንዲት ነጻ ሃገር ኢትዮጵያ -->

Mertule Mariam

 ርዕሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ገዳም


በጎጃም ክፍለ ሀገር ከሚገኙት አያሌ ቅዱሳት ገደማት መካከል ታላቋ እና ጥንታዊቷ ርዕሰ ርኡሳን
መርጡለ ማርያም ገዳም አንዷ ናት። ርዕሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም ገዳም የምትገኘው በጎጃም ክፍለ ሀገር በምሥራቅ ጎጃም ዞን በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ርዕሰ ከተማ መርጡለ ማርያም ሲሆን ከአዲስ አበባ ሰሜናዊ አቅጣጫ ከባሕር ጠለል በላይ በ2,405 ሜትር ከፍታ በቀጥታ ልኬት በወፍ በረር በ128 ማይል ( 206 ኪ.ሜ ) በመኪና መስመር ደግሞ በደጀን ጒንደ ወይን መስመር 364 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በላቲቲዩድ 10°49'60" ሰሜን እና በ38°16'0" ሎንግቲዩድ ምስራቅ ድግሪ ሚኑት ሴኮንድ ወይም በ10.8333 እና በ38.2667 ዴሲማል ድግሪ በመርጡለ ማርያም ከተማ ትገኛለች። ገዳሟ ከአዲስ አበባ ፫፻፷፬(364) ኪ.ሜ፣ ከአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባህር ዳር ፻፹(180) ኪ.ሜ ፣ ከምሥራቅ ጎጃም ርዕሰ ከተማ ደብረ ማርቆስ ደግሞ ፻፺፪(192) ኪ.ሜ እንዲሁም ከዓባይ ወንዝ ደግሞ በግምት 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ወደ ታሪካዊቷ መርጡለ ማርያም ገዳም ለመሄድ ከአዲስ አበባ በመነሳት በደጀን-ቢቸና መስመርከጎንደር ወይም ባህር ዳር በመነሳት በሞጣ መርጡለ ማርያም እንዲሁም ከወሎ በመነሳት በደሴ መካነ ሰላም መስመር በማድረግ ነው። ከወረዳው እነብሴ ሳር ምድር የሚዋሰኑ ቦታዎች ፦

➥በሰሜን፦ ደቡብ ጎንደር ዞን
➥በደቡብ ፦ እናርጅ እናውጋ ወረዳ
➥በምሥራቅ፦ ደቡብ ወሎ ዞን
➥በምዕራብ፦ ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ

መርጡለ ማርያም ትርጉሙ የማርያም አዳራሽ ወይም የማርያም ቤት ማለት ነው። ርዕሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ገዳም አሁን የያዘችውን የስም መጠሪያ ከመያዟ በፊት በተለያዩ ዘመናት አራት ጊዜ የስም መለዋወጦች አጋጥሟታል። መጀመሪያ ሀገረ እግዚአብሔር ትባል ነበር። ቀጥሎ ደግሞ ሀገረ ሰላም ተብላለች። ከዚያም ጽርሐ አርያም ተብላ ተጠርታለች። ትርጉሙም ምድራዊ ሳለች ሰማያዊት ቤት የሆነች ወይም መንግስተ ሰማይን የምታወርስ አዳራሽ ማለት ነው። በመጨረሻም አሁን የምትጠራበትን መርጡለ ማርያም የሚለውን ስያሜ አግኝታለች።

ገዳሟ በኢትዮጵያ መስዋዕተ ኦሪት ሲሰዋባቸው ከነበሩት አራቱ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ናት። መስዋዕተ ኦሪት ሲሰዋባቸው የነበሩ አርባእቱ ( አራቱ ) መናብርተ ጽዮን አክሱም ጽዮን፣ ተድባበ ማርያም፣ መርጡለ ማርያም እና ጣና ቂርቆስ ናቸው። የእነዚህ አራቱ መናብርተ ጽዮን አስተዳዳሪዎች በኢትዮጵያ ካሉ ሌሎች አድባራት እና ገዳማት የተለየ እና ክፍ ያለ ክብር አላቸው። የመርጡለ ማርያም ገዳም አስተዳዳሪ ርዕሰ ርዑሳን የሚል ስያሜ( የማዕረግ መጠሪያ) አለው። በኢትዮጵያ ነገሥታት በሚነግሱበት ጊዜ የገዳሟ አስተዳዳሪ ጠላትህን በእጅህ ጭብጥ በእግርህ እርግጥ አድርገህ ግዛ ብሎ የወርቁን ከዘራ በንጉሡ ቀኝ እጅ ያስጨብጠው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
በገዳሟ ስርዓት መሰረት ርዕሰ ርዑሳን ተብለው እየተሾሙ ገዳሟን ያገለገሉ አስተዳዳሪዎች ስም ዝርዝር፦
1. ርዕሰ ርዑሳን ሚናስ (የኦሪት ሊቀ ካህናት የነበሩ በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ርዕሰ ርዑሳን ተብለው የተሾሙ የመጀመሪያው ርዕሰ ርዑሳን)
2. መምህር ኪዳነ ማርያም
3. መምህር ቢኖር
4. መምህር ወልደ ሴም
5. መምህር ወልደ ሚካኤል
6. መምህር ወልደ ማርያም
7. መምህር እሼቴ
8. መምህር እንግዳ
9. መምህር ክንፈ ሚካኤል
10. መምህር ሳህሉ
11. መምህር ዘውዱ
12. መምህር ወልደ ኤዎስጣቴዎስ
13. መምህር ሐብተ ድንግል
14. መምህር ገብረ ሚካኤል
15. መምህር ፀሐይ
16. መምህር ክንፉ
17. መምህር ካሳ አየለ
18. መምህር ውቤ
19. መምህር ወልደ ጊወርጊስ
20. መምህር አሰገነኝ
21. መምህር ፊላታኦስ
22. ርዕሰ ርዑሳን አባ ላእከ ማርያም አየለ
23. ርዕሰ ርዑሳን አባ ሃይለ ኢየሱስ ገብረማርያም
24. ርዕሰ ርዑሳን አባ ወልደማርያም አማረ
25. ርዕሰ ርዑሳን አባ ሐብተ ሚካኤል ታደሰ
26. ርዕሰ ርዑሳን አባ ኃይለማርያም ታገለ
27. ርዕሰ ርዑሳን አባ ተክለ ማርያም ባዩ
28. ርዕሰ ርዑሳን አባ ወልደ መድኅን ታዴ
29. ርዕሰ ርዑሳን አባ ገብረ ማርያም ገረመው

ከተራ ቁጥር 2 ጀምሮ እስከ ተራ ቁጥር 21 ድረስ የገዳሟ ስተዳዳሪዎች መምህር እየተባሉ የተጠሩበት ምክንያት ደጃዝማች ስዩም በኋላ ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ማለትም ከበዛብህ ተክለ ሃይማኖት ቀጥሎ የተወለደው የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ልጅ ርዕሰ ርዑሳን የሚለውን መጠሪያ ም ስም ለራሳቸው ስላደረጉት ነበር። ነገር ግን ከመምህር ፊላታኦስ ቀጥሎ የተሾሙት አባት ማለትም ርዕሰ ርዑሳን አባ ላእከ ማርያም አየለ ተከራክረው ስያሜውን አስመልሰውታል።

ቪዲዮ፦ የመርጡለ ማርያም ታሪክ
ይህች ታላቅ እና ጥንታዊት ገዳም የተመሰረተችው ከእስራኤሉ ንጉሥ ሰሎሞን እና ከኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ (ማክዳ) የተወለደው ቀዳማዊ ምኒሊክ ይዟቸው በመጣ ፫፻፲፰(318) የኦሪት ካህናት በአራት ሺ አምስት መቶ ዓመተ ዓለም (ከክርስቶስ ልደት በፊት ከአንደኛው ሺህ ዓመተ ዓለም መጨረሻ ማለትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊወለድ አንድ ሺህ ዓመት ሲቀረው) ነው። ወደዚች ቦታ የመጡት የኦሪት ካህናት መሥዋተ ኦሪትን በመሰዋት የኦሪትን አምልኮት ሲፈጽሙ ኖረዋል። በ፫፻፴፫ (333) ዓ.ም ህሩያን ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሃ ከከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ ጋር በመሆን በዚች ቦታ መጥተው ሕገ ወንጌልን አስተምረዋል ሕዝቡን አጥምቀው ካህናትን ሹመዋል።
ገድለ አብርሃ ወአጽብሃ እና ገድለ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን እንደሚያስረዱት ሕሩያን ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሃ ከጳጳሱ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ጋር በመሆን በ፫፻፴፫ ዓ.ም ዓባይን ተሻግረው ጎጃም ምድር መርጡለ ማርያም ደረሱ። ወአደው ፈለገ ግዮን አብርሃ ወአጽብሃ ዘምስለ ሰላማከሳቴ ብርሃን ወበጽሑ ምድረ ጎጃም በዚህ ቦታ ሕዝበ ክርስቲያኑን ወንጌል አስተምረው መክረው ከኦሪት ወደ ሐዲስ ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሰው ካጠመቁበኋላሕዝበ ክርስቲያኑ አምልኮቱን የሚፈፅምበት ቤተ ክርስቲያንን ለመስራት አሰቡ። ቦታው ላይ በጣም የሚያምር ቤተ ምኲራብ ስለ ነበር ይህንን ለታሪክ ትተን ሌላ ቦታ ላይ እንስራ በማለት በስተ ምሥራቅ አሻጋሪ ካለው ተራራ አሁን ግንብ ወሬ እየተባለ ከሚጠራው ኮረብታ ለይ ቁፋሮ ጀመሩ። ነገር ግን መሬቱ የእሳት ትንታግ እየተፋ አልቆፈር አለ። በመሆኑም በዚህ ቦታ ቤተ ክርስቲያን እንሰራ ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀደም ፈቃደ እግዚአብሔርን እናውቅ ዘንድ ለ፫ ተከታታይ ቀናት ሱባኤ እንግባ በማለት በ፭ በአካባቢው ባሉ የተለያዩ ኮረብታዎች ሱባኤ ገቡ። ሱባኤ የገቡባቸው ከረብታዎች የሚከተሉት ናቸው።
፩. የኦሪቱ ሊቀ ካህን አብኒ ቢታንያ ከተባለው ኮረብታ
፪. የሐዲሱ ሹም ሐዲስጌ ከተባለው ኮረብታ
፫. ጳጳሱ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ሰላምጌ ከተባለው ኮረብታ
፬. ንጉሥ አብርሃ ግንቦሬ( ግንብወሬ) ከተባለው ኮረብታ
፭. ንጉሥ አጽብሃ ዜነዎ (የአሁን መጠሪያ ዜኖ) ከተባለው ኮረብታ
ሐዲስጌ፣ ሰላምጌ፣ ቢታንያ እንዲሁም ግንቦሬ የተባሉት ከረብታማ ቦታዎች እስካሁንም ተመሳሳት መጠሪያ ስያሜዎች አሏቸው። ከሱባኤው በኋላ ንጉሥ አጽብሃም ከሁሉም አስቀድሞ ወደ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን በመሄድ ያየውን ራዕይ ተናገረ። ሌሎችም መጥተው ያዩትን ሁሉ ተናገሩ አባ ሰላማም ይህንን ራዕይ ያዩ መሆናቸውን ነገሯቸው። ሁሉም በአንዲት ሌሊት አንድ ዓይነት ራዕይ አዩ። ያዩት ራዕይም ዐሥራ ሁለት በሮች ያላት አንድ አምደ ብርሃን የቤተ መቅደሱ መሰረት ከተጀመረበት ኮረብታ ተነስታ እያበራች የጥንቱ ቤተ ምኲራብ ከሚገኝበት ጽርሐ አርያም አምባ ላይ ስታርፍ የሚያሳይ ነበር። ጧት ወደ ቦታው ሲሄዱ የጥንቱ አስደናቂው ቤተ ምኲራብ መሬት ውስጥ ተቀብሮ ለጥ ያለ አረንጓዴ ሜዳሆኖ አገኙት። ወእም ድህረዝ ፈቀዱ አብርሃ ወ አጽብሃ ከመ ይህንጽ መቅደስ በህየ ወሐነጹ ማህደረ ሰናይተ ወገብሩ አረፋቲሃ ዘወርቅ ወዘብሩር ወሴሙ ካህናተ ወዲያቆናተ ወአስተሳነዩ ኲሎሥርዓተ ወሴሙ በውስቴታ ርዕሰ ርዑሳን ዘውእቱ ሊቀ ካህናት ወሰመይዋ ለይእቲ መቅደስ መርጡለ ማርያም ትርጉም፦ ነገሥታቱ አብርሃ ወ አጽብሃበ ቦታው ቤተ መቅደስን ይሰሩ ዘንድ ወደዱ በወርቅ እና በእንቍ አምዶችን እና አረፍቶችን ልዩ አድርገው በማስጌጥ የማርያምን ቤተመቅደስ ሠሩ። ሥርዓትንም በመደንገግ ካህናትን፣ ዲያቆናትን እንዲሁም ሁሉንም ሊያስተዳድር የሚችል ሊቀ ካህናት ርዕሰ ርዑሳን ብለው ሾሙ። መቅደሷንም መርጡለ ማርያም ብለው ሰየሟት። ንጉሥ አብርሃወ አጽብሃም እግዚአብሔርበመራቸው መሰረት በጳጳሱ በአባ ሰላማ አስባርከው በጽርሐ አርያም አምባላይ አስደናቂውንባለ ፲፪(12) ቤተመቅደስ ባለ ፩ ፎቅ ቤተ መቅደስ ሰርተው በወርቅ፣ በእንቊ እንዲሁም በከበሩማዕድናት አስጊጠው ጥር ፳፩ (21) ቀን የእመቤታችንን ጽላት አስገብተው ቅዳሴ ቤቱን አከበሩ። ንጉሥ አብርሃ ወአጽብሃ ቤተ መቅደስ ለመስራት መጀመሪያ ቁፋሮ የጀመሩበት ተራራ አሁንም ግንብ ወሬ (ግንቦሬ) እየተባለ ይጠራል፤ ትርጉሙም በወሬ የቀረ ግንብ ማለት ነው። በዚህ የተነሳ ንጉሥ አጽብሃ በመጀመሪያ መጥቶ ራዕዩን ስለ ተናገረ ሱባኤ የገባበት ኮረብታ ዜነዎ ሲባል ሌሎች አባቶች ሱባኤ የያዙባቸው ኮረብታዎች አሁንም በየስሞቻቸውእየተጠሩ ሕያው የታሪክ ምስክሮች ሆነው ይገኛሉ።
ይህ ቤተ ክርስቲያን እጅግ የተለየ በልዩ ልዩ ቅርፅ ያጌጠ በወርቅ እና በእንቁ የተለበጠ አስደናቂ የጥበብ አሻራ ያረፈበት ነበር። ይህ ቤተ መቅደስ በዘመኑ በቤተክርስቲያን ጠላትነት በተነሳችው በዮዲት ጉዲት ዘመን በ፰፻፵፪(842) ዓ.ም ተቃጥሏል። ከቃጠሎው የተረፈው ፍርስራሽ አሁንም አለ። በ፰፻፹፪ (882) ዓ.ም የነገሰው አንበሳ ውድም በዮዲት የተቃጠለውን ቤተ ክርስቲያን እንደገና አሰርቶታል። ነገር ግን አብርሃ ወአጽብሃ ያሰሩት ባለ ፲፪ ቤተ መቅደስ እና ባለ ፩ ፎቅ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መልሶ ለመስራት በጣም አስቸጋሪ ሰፊ ታላላቅ ሙያተኞችን የሚጠይቅ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ውስብስብ እና ጥልቅ ጥበብ የሚጠይቅ በመሆኑ መልሶ ለመስራት አልቻለም። በመሆኑም ከተቃጠለው ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ሌላ የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን አሰርቷል። ይህ ቤተ ክርስቲያን አሁንም በአገልግሎት ላይ አለ። ይህንን ቤተ ክርስቲያንን ከነሐሴ ፳፮(26) ፲፬፻፷(1460) ዓ.ም - ኅዳር ፲ ፲፬፻፸ ዓ.ም የነገሠው ንጉሥ ዐፄ በእደ ማርያም በ፲፬፻፷ ዓ.ም አሳድሶታል። ባለቤቱ ንግሥት እሌኒ ደግሞ የአንባውን ዙሪያ አሰርታለች አሁንም የገዳሟ ዙሪያ የእሌኒ ውድሞ ይባላል። ንጉሠ ነገሠት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በ፲፱፻፴፯(1937) ዓ.ም ሌላ ቤተ ክርስቲያን በዚች ገዳም ውስጥ አሰርተዋል። የቅድስት ሥላሴ እና የቅዱስ ገብርኤል ጽላት ይገኝበታል። እንደገናም በ፲፱፻፸፫(1973) ዓ.ም በወቅቱ የገዳሟ አስተዳዳሪ የነበሩት ርዕሰ ርዑሳን አባ ለእከ ማርያም ከሳር ክዳን አሁን ወዳለበት ቆርቆሮ ክዳን አሳደሰውታል። በዚች ገዳም ውስጥ ፫ ቤተ ክርስቲያን አሉ።
፩. አብርሃ ወ አጽብሃ ያሰሩት የእመቤታችን ቤተ መቅደስ
፪. ነጉሥ አንበሳ ውድም ያሰራው የእመቤታችን ቤተ መቅደስ
፫. ንጉሥ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ያሰሩት የቅድስት ሥላሴ እና የቅዱስ ገብርኤል ቤተ መቅደስ ናቸው።

መርጦ ለማርያም በምሥራቅ ጐጃም ዞን ከሚገኙ ገዳማት እና አድባራት ቀዳሚና ብዙ የቅርስ ክምችት ካለባቸው ገዳማት ውስጥ አንዷት ናት። ገዳሟ በዋጋ የማይተመን ከፍተኛ የቅርስ ክምችት ያላት ናት። በመርጡለ ማርያም ሙዚየም ውስጥ ከሚገኙ ውድ ቅርሶች ውስጥ፦
⇨ የአብርሃ ወአጽብሃ የወርቅ መስቀል፣
⇨ ሙሴ ያመጣው ባለ ስድስት ገፅ የድንጋይ ሀውልት
⇨ በ፬፻፵፭(445) ዓ/ም የተጻፈ ግእዙን በግእዝ የሚተረጉም አርባዕቱ ወንጌል፣
⇨ የአጼ በእደ ማርያም ራስ ቁርና የወርቅ ለምድ፣
⇨ የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘውድ፣
⇨ የንግሥት እሌኒ የክብር ካባና የብር ዋንጫ፣
⇨ የአጼ ገላውዲዎስ እና የእናቱ የሰብለውንጌል የክብር ልብስ፣
⇨ በ ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአጼ ዮሐንስ የተበረከተ ራሱን ችሎ መቆም የሚችል ባለ ሦስት እግር የወርቅ መስቀል፣
⇨ አፍሮ አይገባ የብር መስቀል፣
⇨ ልዩ ልዩ የብርና የወርቅ መስቀሎች፣
⇨ ልዩ ልዩ የወርቅ አክሊሎች፣
⇨ የራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ከብርና ከወርቅ የተሰራ ከበሮ፣
⇨ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ አባቶች የተበረከቱ ነጋሪቶች፣
⇨ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የፍርድ መስጫ ዙፋን፣
⇨ የብር መነሳንሶች፣
⇨ የአጼ ገላውዲዮስ ዳዊትና ካባ፣
⇨ የኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም (አህመድ ግራኝ) የክብር ካባ፣
⇨ በገበታ ላይ የተሳሉ ጥንታዊ ስዕላት፣
⇨ የመሳፍንቶችና የመኳንቶች በወርቅና በብር ያጌጡ የክብር ልብሶች፣
⇨ የብራና መጻሕፍት እና የመሳሰሉትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ምስል ፦ መርጡለ ለማርያም ገዳም፣ የመርጡለ ማርያም ገዳም በር እና የመርጡለ ማርያም መስኮት
ምስል፦ በመርጡለ ማርያም ገዳም ከሚገኙ ቅርሶች ውስጥ በጥቂቱ

ምስል ፦ የጥር ፳፩( አስተርእዮ ማርያም) በዓል አከባበር በመርጡለ ማርያም ገዳም


አዘጋጅ፦  የባሕል ክፍል

የአማራ ትስስር በቻይና


ጥር 21   2015 ዓ.ም 

ቻይና

የአማራ ትስስር በቻይና(ANiC)

የአማራ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ፣ ሃይማኖትና ባህል ያለው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት የሆነ፤ ሃገር የሰራ፣ ነጻነቱን ያስጠበቀ፤ የራሱ የሆነ ፊደል ያለው፤ የጥንታዊ ትምህርት ስርዓት ባለቤት የሆነ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ በሃገረ መንግስት ምስረታ ሃገርን ከወራሪ መጠበቅና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ታላቅ ገድል በመስራት እኛ ልጆቹ ቀና ብለን እንድንሄድ አድርጎናል።

1 Comments

ቀዳሚ ገጽ ተከታይ ገጽ
hi