ይህ የአማራ ትሥሥርር በቻይና ይፋዊ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ድረ-ገጽ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ልማድ፣ አርበኝነት፣ ቅርስ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችንም ጭምር ለአባላት በሚገባ እናሳውቃለን። የድረ-ገጹ ዋና አላማ የአማራን ታሪክ በሚገባ ለሁሉም በማስተማር ታሪካችንን ወደቀደመ ልዕልናው መመለስ ነው። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤ አንዲት ነጻ ሃገር ኢትዮጵያ -->

ንጉሥ ላሊበላ (King Lalibela)

 ንጉሥ ላሊበላ 

የንጉሥ ላሊበላ ገድል ስለትውልዱ እንዲህ ይላል፦  አባቱ በላስታ አውራጃ የቡግናው ገዢ የነበረው ዣን ስዩም ሲሆን እናቱ ኪርወርና ደግሞ አገልጋይ ነበረች። አገልጋይቱ ከዣን ስዩም ማርገዟን የሰማችው የዣን ስዩም ሚስት በንዴት ጦፈች።  እመቤቲቱን ፍራቻ ነፍሰጡሯ አገልጋይ ወደ ሮሃ  የዛሬዋ ላሊበላ  ሸሽታ ሕፃኑ እዚያ ተወለደ። እናቲቱ ሕፃኑን እዚያው ትታ ወደ ዣን ስዩም ቤት ተመለሰች። ሕፃኑን ፍለጋ ዣን ስዩም ሰዎች ወደ ሮሃ ሲልክ ሕፃኑ በንቦች ተከብቦ አገኙት። ይሄኔ ሰዎቹ፦ ላህሊ..በላ አሉ፤ ንቦች ታላቅነቱን ተረዱለት እንደማለት ነው (ገድለ ላሊበላ)።  የቅዱስ ላሊበላ የትውልድ ቀን ታኅሣሥ  ፳፱ ቀን ፲፩፻፩( ታኅሣሥ 29 1101) ዓ.ም ሲሆን በየዓመቱ ታኅሣሥ  ፳፱(29) የገና ዕለት በስሙ በተሰየመችው በቀድሞዋ ሮሃ በአሁኗ ላሊበላ ታላቅ ክብረ በዓል ይሆናል። የልደቱን ነገር አስቀድሞ ቅዱስ ሚካኤል ለእናቱ ነግሯት ነበር፤ ከላይ በገድለ ላሊበላ እንደተጠቀሰው ቅዱስ ላሊበላ በተወለደ ጊዜም ብዙ ነጫጭ ንቦች መጥተው በሰውነቱ ላይ አርፈው እንደ ማር እየላሱት ስለታዩ እናቱ ልጄን ንብ ዘበኛ ሆኖ ይጠብቅልኛል ስትል ስሙን ላል ይበላል ብላዋለች። ላል በአገውኛ ንብ ማለት ነው። በጊዜ ብዛት በተለምዶ ላሊበላ ተብሎ መጠራት ተጀመረ። አባቶች እንደሚሉት  ንቦቹ ሥጋዊ ንቦች ሳይሆኑ በንብ የተመሰሉ መላእክት ናቸው። ንጉሥ መሆኑን እያመለከቱ ሃይማኖትና ምግባር ማር ከእርሱ እንደሚቀዳ ለማመልከት በንብ ሠራዊት ተመስለው ሰውነቱን ላሱት። እንደ ዮሐንስና እንደ ኤርምያስም በእናቱ ማኅፀን ሳለ  መንፈስ ቅዱስ የሞላበት እንደሆነ ይነገርለታል። 

የላሊበላ ወንድም ሀርቤ ለአባቱ ዙፋን ከላሊበላ ይልቅ የተገባ በመሆኑ  ከህጋዊ ሚስት የተወለደ እንደመሆኑ መጠን እና ከላሊበላ ጋር ተያይዞ በሚነሳው ትንቢት ሳቢያ ወንድሙን በበጎ አላየውም። በዚህም የተነሳ ላሊበላ ሀገሩን ለቅቆ ወደ እየሩሳሌም አቀና።  በዚያም ለብዙ ዓመታት ቆየ። ከስደት እንደተመለሰ  መስቀል ክብራን አገባ።  ቢሆንም ግን ወንድሙ ሀርቤን ፍራቻ ወደ በረሃ ለመሰደድ ተገደደ። ስለ ላሊበላ ወደ ዙፋን አወጣጥ የሚጠቀሱት ዘገባዎች የተለያዩ ናቸው። አንድ ምንጭ  ሀርቤ የላሊበላን መንገስ አይቀሬነት ስለተገነዘበ ዙፋኑን ለላሊበላ ለቅቆ ገብረመስቀል ብሎ አነገሰው( ዝርዝሩ እንደሚናገረው ቅዱስ ላሊበላ ከስደት እንደተመለሰ ወንድሙ መልእክቶኞችን ልኮ ካስመጣው በኋላ ምክንያት አድርጎ ከሦስት እስከ ሰባት ሰዓታት ያህል እንዲገረፍ አደረገ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ከግርፋቱ ሠውሮት ስለነበር ምንም ጉዳት አልደረሰበትም። ወንድሙም ከፊቱ ባቆምመው ጊዜ ይህን ተአምር አይቶ ከመኳንንቶቹ ጋር አደነቀ። ይቅርታ እንዲያደርግለትም ቅዱስ ላሊበላን ጠይቆት እርቅ ሆነ።  ከዚህም በኋላ ላሊበላ  መስቀል ክብራን አገባ። ወንድሙም የእርሱን መንገሥ አይቀሬነት ሲረሳ ዙፋኑን ለወንድሙ ለቀቀ። ንጉሡም  በ፲፻፩፻፶፮ ዓ.ም ገብረ መስቀል ተብሎ ነገሠ)ሲል፤ ሌላኛው ደግሞ በጦርነት ላሊበላ ወንድሙን አሸንፎ ዙፋኑን እንደወረሰ  ይገልጻል። የሆነው ሆኖ ላሊበላ በ፲፩፻፶፮  (1156) ዓ.ም  ገብረመስቀል ተብሎ ነገሠ።  ለ(40) ዓመታትም ገዛ። በዘመነ መንግሥቱም ዘወትር ለድሆችና ለምስኪኖች እንዲሁም ለችግረኞች ይመጸውት እንደነበረ ታሪክ ያስረዳል። በአንድ ወቅትም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት ወደ ሰማያት አወጣው፤ ዐሥሩን አብያተ ክርስቲያናትንም እንዴት መሥራት እንደሚችል አሳየው። ወደ ምድርም ተመልሶ መንፈስ ቅዱስ እንዳረቀቀው በአስደናቂ ጥበብ አብያተ ቤተ ክርስቶያናቱን አነጻቸው

ላሊበላ ያስተዳድረው የነበረው ግዛት እጅግ ሰፊ እንደነበር ይነገራል። ይኸውም  ከአባይ እስከ ምፅዋከወንጪት እስከ መተማከሐረር እስከ ዘይላከጅማ እስከ ጫጫ ከሲዳሞ እስከ ነጭ አባይ ይዘረጋል። ንጉሥ ላሊበላ ይህን ሰፊ ግዛቱን በአራት ከፍሎ በአራት አስተዳዳሪዎች ያስተዳድር የነበረ ሲሆን፤ አቡ ሳሊህ የተባለ የወቅቱ ፀሐፊ የላሊበላን ግዛት በተመለከተ በዓለም ካሉ አራት ታላላቅ ነገሥታት አንዱ … የትኛውም ንጉሥ ክንዱን አይቋቋመውም ብሎለታል።  ላሊበላ በንግሥና ዘመኑ ከሌሎች ሀገራት ጋር መልካም ወዳጅነትን ፈጥሮ ነበር። በወቅቱ ከግብጽ ጋር ተቋርጦ የነበረው የንግድ ግንኙነት ተጀምሯል። በግብጽ በነበሩት ክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው መከራም ጋብ ብሏል።

መንፈሳዊው ንጉሥ ላሊበላ ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱና ዋንኛው በዘመኑ ከአንድ ወጥ ድንጋይ ያስፈለፈላቸው አስራአንድ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱ በሦስት መደብ የተከፋፈሉ ሲሆኑ፤ ሁሉም የመሬት ውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ ያላቸው ናቸው። በመጀመሪያው መደብ ውስጥ፣ ቤተ መድኃኒዓለም(ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ)ቤተ ማርያም(ሰሜን  አቅጣጫ)ቤተ-መስቀል(ሰሜን አቅጣጫ)ቤተ-ደናግል(ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ)ቤተ-ጎለጎታ(ሰሜን አቅጣጫ)እና ቤተ-ሚካኤል(ሰሜን አቅጣጫ)ሲገኙ፤ በሁለተኛው መደብ ውስጥ ደግሞ  ቤተ-አማኑኤል(ምሥራቅ አቅጣጫ)ቤተ-መርቆሪዮስ(ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ)ቤተ-ሊባኖስ(ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ)እና ቤተ-ገብርኤል(ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ)ይገኛሉ። 


ምስል፦ የላሊበላ ከፍልፍል ድንጋይ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያኖች
በሦስተኛው መደብ ውስጥ የሚገኘው ቤተ-ጊዮርጊስ ( በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኘው) ነው። ቤተ-ጊዮርጊስ ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በስተመጨረሻ የተሰራና እጅግ ያማረ በኪነ ህንፃ ውበቱም ከሁሉም የላቀ ነው። ይህም  የአብያተ ክርስቲያናቱ ሠሪዎች በሥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቁ የመምጣታቸው ምስክር ነው። አብዛኛውን ጊዜም የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሲወሱ የሚታየው ምስል የዚሁ የቤተ-ጊዮርጊስ ምስል ነው።
ምስል፦ ቤተ ጊዮርጊስ
ገድለ ላሊበላ እንደሚያስረዳው የፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱ ስራ የተጀመረው በላሊበላ ዐሥረኛ ንግሥ ዘመኑ ነው።  ሥራውን ለማጠናቀቅም ፳፫(23) ዓመት ፈጅቷል ይላል ( ገድለ ላሊበላ)። አብያተ ክርስቲያነቱንም አንጾ ከጨረሰ በኋላ መንግሥቱን ለወንድሙ እንዳወረሰው ታሪክ ያስረዳል። 

በአጠቃላይ ቅዱስ ወንጉሥ ላሊበላ ፡-

፩. በብሥራተ መልአክ የተወለደ ነው።

፪. ቅዱሳት መጻሕፍትን ገና በልጅነቱ ያጠና ቅዱስ ነው። 

፫. የንጉሥ ዘር ቢሆንም በጾምና ጸሎት በትሕርምት ያደገ ነው። 

፬. በወንድሙ ቢገረፍም ምንም ቂም አልነበረውም።

፭. ስለ ወዳጆቹ ፍቅር መርዝ ጠጥቷል።

፮. በዙፋን ላይ የኢትዮዽያ ንጉሥ ሆኖ ቢቀመጥም አኗኗሩ ገዳማዊ ነበር።

፯. ከተባረከች ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ጋር አንዲት ማዕድ ብቻ በቀን ይቀምሱ ነበር። ለዚያውም ለምለሙን ለነዳያን ሰጥተው እነርሱ የሚበሉት የእንጀራውን ቅርፍት (ጠርዝ) ብቻ ነበር።

፰. በአካለ ሥጋ ወደ ሰማያት ተነጥቆ ብዙ ምሥጢራትን አይቷል። በምሳሌውም ሃገረ ሮሃን (ላሊበላን) ገንብቷል። ዛሬም ድረስ ምሥጢር የሆኑት ፍልፍል አብያተ መቅደስ የእጆቹ ሥራዎች ናቸው። ሥራውን ከፈጸመ በኋላ መንግሥቱን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አውርሶ በመንኖ ጥሪትና በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል። 

፱. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስምህን ያከበረ ዝክርህን የዘከረ ከቤትህ ያደረውን ከርስተ መንግሥተ ሰማያት አካፍለዋለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል።

፲. ቅድስናን ከንግሥና፤ ቤተ ክህነትን ከቤተ መንግሥት አስተናብረው መምራት ከቻሉ ቀደምት ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ነው።

ቅዱስ ወንጉሥ ላሊበላ በተወለደ በ ፺፯(97) ዓመቱ ሰኔ ፲፪ (12) ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል


የአማራ ትስስር በቻይና

ጥር 3   2015 ዓ.ም 

ቻይና

የአማራ ትስስር በቻይና(ANiC)

የአማራ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ፣ ሃይማኖትና ባህል ያለው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት የሆነ፤ ሃገር የሰራ፣ ነጻነቱን ያስጠበቀ፤ የራሱ የሆነ ፊደል ያለው፤ የጥንታዊ ትምህርት ስርዓት ባለቤት የሆነ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ በሃገረ መንግስት ምስረታ ሃገርን ከወራሪ መጠበቅና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ታላቅ ገድል በመስራት እኛ ልጆቹ ቀና ብለን እንድንሄድ አድርጎናል።

Post a Comment

ቀዳሚ ገጽ ተከታይ ገጽ
hi