ጥንታዊቷ የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርሲቲያን
የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከታሪክ ጸሐፊዎች እይታ አኳያ
ግድግዳዎቹ በጥርብ ድንጋይ ተሠርተው በሐረግ አጊጠዋል፤ የዋናው በር መዝጊያ በወርቅና በብር ተለብዷል፤ በወርቁ ልባድ ውስጥ አንዳንድ የከበሩ ድንጋዮች አሉ። ጣሪያዎቹ በስድስት ምሰሶዎች ላይ ዐርፈዋል። የውጭ ታዛውን 13 ረጃጅም ምሰሶዎች ደግፈውታል። በሠገነቱ ዙሪያ እያንዳንዳቸው ከ16 ቅጽ ወርቀ ዘቦ ጨርቅ የተሠሩ 16 ተከፋች መጋረጃዎች አሉት።
በአሕመድ ኢብን ኢብራሒም አልጋዚ(ግራኝ አሕመድ) የሚመራው የሙስሊሞች ሠራዊት የዐፄ ልብነ ድንግልን ጦር ድል አድርጎ የያኔዋን ዋስል የዛሬዋን ወረኢሉ በመቆጣጠር የመካነ ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ከማጥፋት ቀደም ብሎ (ከ1524 ዓ.ም በፊት) የቤተ ክርስቲያኒቱን ገጽታ በብዕሩ የከተበው የግራኝ አሕመድ ታሪክ ጸሐፊ ዓረብ ፋቂህ እንዲህ ሲል ገልጽዋታል። በዚህ በቤተ አምሐራ በሐበሻ ምሳሌ የሌላት አንዲት ቤተ ክርስቲያን አለች። እርሷን የሠራት የወናግ ሰገድ (ልብነ ድንግል) አባት ንጉሥ ናዖድ ነው። የእርሷ ሥራና ጌጥ 13 ዓመት ፈጀበትና ሳይጨርሳት ስለ ሞተ ልጁ ወናግ ሰገድ ከአባቱ አስበልጦ 25 ዓመት ሙሉ አሠርቶ አስጨረሳት። ሁለመናዋ በወርቅ የተለበደ ስለሆነ እንደ እሳት ታንጸባርቃለች፤ በውስጧ ያለው ጻሕል፣ ሰንና ብርት የወርቅና የብር ነው። ስፋቷ መቶ ክንድ ቁመቷ ግን ከመቶ ሃምሳ ክንድ ይበልጣል። ሁለመናዋ በጌጠኛ ዕንጨትና ድንጋይ በወርቅና በከበረ ድንጋይ የተለበደ ነው። ስሟ በክርስቲያኖች ቋንቋ መካነ ሥላሴ ትባላለች። በዚህች ቤተ ክርስቲያን የዘርዐ ያዕቆብ የልጅ ልጅ የአድማስ ሰገድ (በእደ ማርያም) ልጅ የናዖድ መቃብር አለ።ያቺ በሥነ ሕንፃዊ ጥበቧና በተሠራችበት የከበሩ ድንጋዮች ወደር ያልተገኘላት የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በኅዳር ሰባት ቀን 1524 ዓ.ም በግራኝ አሕመድ ፊት አውራሪነት እንድትዘረፍና እንድትቃጠል እንደ ተደረገች ዓረብ ፋቂህ ጽፏል። ግራኝ አሕመድ ቤተ ክርስቲያኗ እንድትዘረፍና እንድትቃጠል ከማዘዙ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥነ-ሕንፃ ማድነቁን ዓረብ ፋቂህ አልሸሸገም። ይህንን የመሠለ የወርቅ ሐውልት ያለበት በወርቅ የተሠራ ቤተ ክርስቲያን በሕንድ በሮም (በቤዛንታይን) ግዛት ዐይታችሁ ታውቃላችሁ? ብሎ በዙሪያው ያሉትን ዓረቦች መጠየቁን የሚያትተው ዓረብ ፋቂህ፡- ይህንን የመሰለ በሮምም በሕንድም ዐይተንም አለ ሲባልም ሰምተን አናውቅም፤ በዓለምም የለም ብለው መለሱለት ሲል ጽፏል። ሆኖም አልቫሬዝ የመካነ ሥላሴ ሕንፃ የማእዘን ድንጋዮች ትናንሽና በደረቅ ካብ የተሠሩ በመኾኑ የጣሪያው መዋቀሪያ እንጨት በግድግዳው እንደማያልፍ ገልጦ፣ ከቤተ ክርስቲያኗ የሚበልጡ ሕንፃዎችን በአውሮፓ ማየቱን ቢያትትም የመካነ ሥላሴ ሕንፃ ጥበብ ግዙፍነትና በከበረ ድንጋይ ያጌጠች እንደነበረች አረጋግጧል። ይህ የሚያመለክተው የመካነ ሥላሴ ጥንታውያት ቤተ ክርስቲያን እንደ ላሊበላ ውቅር ሕንፃዎች፣ እንደ ዐፄ ፋሲል (ጎንደር) ቤተ መንግሥታት ሁሉ በወቅቱ የነበሩትን ኢትዮጵያውያንን የሕንፃ ጥበብ የሚያሳይ አሻራ ነው። የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በላሊበላ ውቅር አቤተ ክርስቲያናት በተሠሩበት ዘመንና በጎንደር የፋሲል አብያተ መንግሥታት የተሠሩበት ዘመን መካከል መገኘቱ ያ የኢትዮጵያውያን የሥነ ሕንፃ ጥበብ ቀጣይነት እንደነበረው ጠቋሚ ሊሆን ይችላል።
ከግራኝ አሕመድ ሠራዊት ዘረፋና ቃጠሎ የተረፈው የቤተ መቅደሱ የመሠረት ግንብ የቅድስቱና የቅኔ ማኅሌቱ መለያ ግንቦች በዕድሜ ጫና ጥበቃና ክብካቤ በማጣት እየፈራረሱ ወደ አፈርነት እየተለወጡ ለዘመናት ቆይተዋል።
የመካነ ቅርሱ አሠራርና መጠን
በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምዕራብና በምሥራቅ በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያስገቡ አራት ደረጃዎች እንደነበሩት ታውቋል። በሰሜንና በደቡብ በኩል ያሉት ደረጃዎች አራት ሜትር ቁመትና ሦስት ሜትር ጎኖች ያሏቸው ሲሆን በምዕራብና በምሥራቅ በኩል የነበሩት ደረጃዎች ወድመዋል። በቤተ መቅደሱና በቅድስቱ ወለል እስከ መሠረቱ ግንብ ጥልቀት ባለው ሁለት ሜትር ቁመት ላይ የዘመኑን የሥነ ሕንፃ ምሕንድስና ጥበብ የሚያንጸባርቁ የተለያዩ ጌጣጌጦች ይታያሉ። እነዚህም ጌጣጌጦች የሐረግና የተለያዩ አበባዎች ቅርጾችን እንዲሁም የተለያዩ ምስሎችን ይዘው ይገኛሉ። በሌላ በኩል በጥንታዊው የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ቤተ መቅደስ ወለል ላይ በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ተሠራች ተብሎ በአካባቢው ነዋሪዎች የሚነገር አንዲት አነስተኛ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ቆማ ትገኛለች። ቤተ ክርስቲያኗ መጀመሪያ ስትሠራ በሣር የተከደነች እንደነበረችነ በኋላ ግን የሣሩ ክዳን ተነሥቶ ቆርቆሮ መልበሷን ግድግዳዋ ግን ሳይነካ ቀድሞ በነበረበት ሁኔታ ላይ እንዳለ ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ። የቤተ ክርስቲያኗ ግድግዳ ከድንጋይ የተሠራ ሆኖ ከእነዚህ የግድግዳ ድንጋዮችም የጥንቱ የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል። ይህች ቤተ ክርስቲያን እስከ አሁን ድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደምትገኝ በግልፅ ታውቋል።
መካነ ቅርሱ አሁን ያለበት ሁኔታ
የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስያን ቅሪት ከ485 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩ ቅርሱን ዕድሜ ጠገብ የሚያደርገው ሲሆን የሥነ ሕንፃው ምሕንድስና እና ጥበብ በዘመኑ ከነበሩት የተለየ ነው። ጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን ከአብዛኞቹ ጥንታዉያን አብያተ ክርስቲያናት በተለየ መልኩ ሰፊና ግዙፍ መሆኑ ራሱ ልዩ ያደርገዋል። ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራበት ጥሬ ዕቃ (ገህ ድንጋይ) በአካባቢው በቅርብ ርቀት አለመገኘቱና በሌሎች በአካባቢው ባሉ አቤያተ ክርስቲያናት ጥቅም ላይ ውሎ አለመታየቱ ቤተ ክርስቲያኑ በጥንቃቄና ታስቦበት የተሠራ መሆኑን ይጠቁማል። ቤተ ክርስቲያኑን ለመሥራት የፈጀው ዓመትም ረዥም መሆኑ የቤተ ክርስቲያኑን ታሪክ ልዩ ያደርገዋል። ይህንን ሁሉ ዘመን ከዚያም በኋላ ያለውን ጊዜ የሚጠቁሙ አርኪዎሎጂያዊ ታሪካዊና ባህላዊ መረጃዎችን ሸሽጎ መያዙ አይቀሬ በመሆኑ እነዚህም መረጃዎች የማዳን ተግባር አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው። በቅርሱና በአካባቢው የተካሄደውን የቅኝት ሥራ ውጤት መሠረት በማድረግ ሥራ በማከናወን የቤተ መቅደሱን መሠረት ዙሪያና ወለሉን በማጽዳት በወለሉ ላይ የነበሩ የመስቀል ቅርጽ የነበራቸው 26 ወንበሮች በጎለህ እንዲታዩ ሆነዋል። የሙከራ ቁፋሮ ተካሂዶ የቤተ መቅደሱ የመሠረት ግንብ ጥልቀት ምን ያህል እንደሆነ ተረጋግጧል። የቤተ መቅደሱን የቅድስቱንና የቅኔ ማኅሌቱን የግንብ መጠን በመለካት መጠነ ዙሪያቸውን ስፋታቸውንና ርዝመታቸውን ለማወቅ ተችሏል። የቅኝት ስልቱን ውጤት በመንተራስ የዘመሙና ሊወድቁ ተቃርበው የነበሩ የቤተ መቅደሱ መሠረት ድንጋዮችን በደረቅ ካብ በመካብ ደግፎ በጊዜያዊነት እንዲያቆያቸው ተደርጓል። ይህም ተግባር ቅርሱ አጠቃላይ ጥገና እስከሚካሄድበት ድረስ ጊዜያዊ ድጋፍ እንደሚሆነው ይታመናል። የቅኝቱንና የአሰሳውን ስልት መሠረት በማድረግ የተጎዳውን የቤተ ክርስቲያኗን ፍርስራሽ ክፍል ደኅና ከሚባለው ለመለየት ተችሏል። ባለ ማወቅ ተቆፍረው ለጥፋት ተዳርገው የሚገኙትን የቤተ መቅደሱን ክፍሎች አፈር በመመለስ ለዝናብ፣ ለፀሐይ፣ ለሰውና ለእንስሳት ተጋልጠው ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ተችሏል። በጣም ጉዳት ደርሶበት ያለው ምሥራቃዊው የቤተ መቅደሱ ጎን አፈሩ በዝናብ ታጥቦ (ተሸርሽሮ) ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስበት ድንጋይ የማልበስ ሥራ ተሠርቷል። በተጨማሪም በዚሁ በምሥራቃዊው ጎን ላይ ተከማችተው የነበሩ ለሕንፃው ባዕድ የሆኑ ድንጋዮች ከሥር ያለውን የመሠረት ድንጋይ ስለ ጎዱት ከቦታቸው በማስወገድ ከቤተ መቅደሱ እስከ ቅድስቱ መለያ ግንብ ድረስ ታጥሮ የነበረውን የድንጋይ ካብ በማንሣት ለሰዎች መተላለፊያ እንዲሆን በማስቻል ምእመናን በፍርስራሹ ላይ እንዳይረማዱ ማድረግ ተችሏል። ለአካባቢው ማኅበረሰብ ስለ ቅርሱ ምንነትና ጠቀሜታ እንዲሁም እንክብካቤና ጥበቃ ብሎም ለወደፊት ስለሚያስገኘው ኢኮኖሚ (ግንዛቤ) በማስጨበጥ ኅብረተሰቡ ጠቃሚ ትምህርት (መረጃ) እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል። ከላይ ከተጠቀሰው ጋር በተያያዘ መካነ ቅርሱን የሚጠብቅና የሚንከባከብ ዘጠኝ አባላትን ያቀፈና ከተለያዩ የኅብረተሰቡና የመንግሥት አካላት የተውጣጣ የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ጥበቃና ክብካቤ ኮሚቴ ማቋቋም ተችሏል።