ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያምና ግማደ መስቀሉ
ስቡሕኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ ለዓለም፤
ንፍሑ ቀርነ በጽዮን፤ ስብኩ በዓለ ማርያም
ወበዓለ መስቀል ዘዮም።
መስከረም ፳፩ ቀን የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ዓመታዊ ንግሥ ነው። የአማኑኤል ግማደ መስቀሉ፤ ግሸን ነው አሉ። ይላሉ ተጓዥ ምእመኑ። ግሸን ጌሰ ፡ ገሰገሰ ከሚለው ቃል በጊዜ ብዛት የወጣ ነው። መገስገሱ ስለምን ነበር ቢሉ፤ አጼ ካሌብ የናግራንን ሰማእታት ለመታደግ በዘመቱ ጊዜ ካገኟቸው ከግሪካዊው ካህን ከአባ ፊሊክስ/ፍቃደ ክርስቶስ ጋር ከናግራን ተራራ፣ ዛሬ በግሸን የሚገኙትን የቅድስት ድንግል ማርያምንና የመድኃኔዓለምን ሁለት ጽላቶች ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። እግረ መንገድም ንጉሡ ስለ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በምስር (ግብጽ) ምድር መገኘት ሰሙ።
መስከረም ፲፮ እና ፲፯ የምናከብረውን የዓመታዊውን የመስቀል ክብረ በዓል፤ የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛው መስቀል መገኘት ታሪክ ከብዙ በጥቂቱ በጨረፍታ እንደሚከተለው በ፫፻፳፮(326) ዓ.ም በዘመኑ ኃያል ገዢ የነበረው የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ፤ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች። በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና በአዛውንቱ አባ ኪራኮስ ምክርም ከኢየሩሳሌም ከተማ ወጣ ብላ፤ መስከረም ፲፮ እንጨት አስደምራ በላዩ ላይ እጣን ስትጨምርበት፤ የደመራው ጪስ ወደ ላይ ወጥቶ ያረፈበትን ኮረብታማ ስፍራ መስከረም ፲፯ ቀን ማስቆፈር ጀምራ፣ በሰባተኛ ወሩ መጋቢት ፲ ቀን መስቀሉን ከተቀበረበት አስወጣችው። ቆይቶም፤ መስቀሉን የዓለም ገናና ነገሥታት ከአንዱ አገር ወደ ሌላው በኃይል ሲናጠቁት፤ የጠቡን መክረር ለማስቆም የኢየሩሳሌም፣ ቁስጥንጥንያ፣ አንጾኪያ፣ ኤፌሶን፣ አርመንያ፣ ግሪክ፣ እስክንድርያ እና ሌሎች አገራት መስቀሉንና ሌሎች የክብር ንዋየ ቅዱሳትን በእጣ ሲካፈሉ፤ ለአፍሪካ የደረሰው የቀኝ ክንፉ ግማደ መስቀል ወደ ግብጽ እስክንድርያ ተወሰደ።
አጼ ካሌብ መስቀሉን እንዲሰጧቸው አለዚያ ግን የአባይ ወንዝን እንደሚገድቡት ለምስር /ግብጽ በዛቻ አስጠንቅቀው ነበር። በእርሳቸው በተተኩት ልጃቸው በአጼ ዳዊት መስቀሉ ከግብጽ ሲመጣ፤ መሀል ሀገር ሳይደርስ አጼ ዳዊት በድንገት ኑቢያ/ሱዳን ምድር ያርፋሉ። ልጃቸው አጼ ዘርዐ ያዕቆብ በተራቸው መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው ቤተ መቅደስ አሰርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ ፤ የራእይ ቃል በህልም እየመጣ አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል!(መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አስቀምጥ!) ይላቸው ጀመር። ከተከታዮቻቸው ጋር ሆነው መስቀለኛውን ስፍራ ፍለጋ መላውን ኢትዮጵያ ሲያዳርሱ ቆይተው በመጨረሻ፤ በወሎ አምባሰል (የማር አምባ) ተራራ አናት ላይ በልዩ አፈጣጠሩ መስቀለኛ ሆኖ ወደሚታየው ተአምረኛ ስፍራ አጼ ዘርዐ ያዕቆብና እኅታቸው ንግሥት እሌኒም እየገሰገሱ መጥተው፤ ግማደ መስቀሉን በዚህ አኖሩት። በርግጥም ይህች ግሽን የተባለች አምባ ጥበበኛ ሰው እንደቀረፃት የተዋበች መስቀልኛ ቦታ ሁና ስለአገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው። በዚያችም አምባ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳቱን በየማዕረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጧቸው ዘመኑም በ፲፬ኛው ክፍለ ዘመን ነው።
ከእስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው የመጡትም ዝርዝር
- ጌታ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ ከሮም የመጣ ከለሜዳው
- ከአፍርጌ ሀገር የመጣው ሐሞት የጠጣበት ሰፍነጉ
- ዮሐንስ የሳለው የኲርዓተ ርዕሱ ስዕል
- ቅዱስ ሉቃስ የሣላቸው የእመቤታችን ስዕሎች
- የበርካታ ቅዱሳን አጽምና በኢየሩሳሌም ውስጥ ከልዩ ልዩቅዱሳት መካናት የተቆነጠረ የመሬት አፈር
- የዮርዳኖስ ውሃ
- በግብጽ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረ አፈር ናቸው።
የእነዚህንም ዝርዝር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለግሼን ካህናት መስከረም ፳፩ ቀን ፩ ሺ ፬፻፵ ዓ.ም ላይ ተናገሩ።
ግሸን ደብረ ከርቤ መጀመሪያ የተመሰረተችው በዘመነ አክሱም በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ሲሆን፤ በወሎ ክፍለ ሃገር አምባሰል ወረዳ ውስጥ ግሸን ተራራ አናት ላይ የምትገኝ ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተክርስቲያን ናት። ጥንታዊነቷም ዓጼ ዘርአ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው ከመምጣታቸው ከ፱፻፴፪(932) ዓመታት በፊት፣ ቅዱስ ላሊበላም ደበረ እግዚአብሔርን ከመመስረቱ ከ፭፻፹፫(583) ዓመት በፊት፣ እነ አባ ኢየሱስ ሞዓ ሃይቅ ደብረ ነጎድጓድን ከመመስረታቸው ፫፻፵፱(349) ዓመት አስቀድሞ በደገኛው አባት እና ለዓጼ ካሌብ እንደ ነፍስ አባት የንስሐ አባት ሆነው የሚያገለግሉት አባ ፍቃደ ክርስቶስ የሚባሉት መንፈሳዊ መናኝ የተመሰረተች መሆኗ ነው። አባ ፈቃደ ክርስቶሥ በ፭፻፲፯(517) ዓ.ም በተራራው ላይ ወጥተው መጠነኛ ጎጆ በመቀለስ ሁለቱን ጽላቶች አስቀመጡ። ሁለቱ ጽላቶችም ታቦተ ቅድስት ድንግል ማርያም እና ታቦተ እግዚአብሔር አብ ናቸው።
ወደዚች ቤተክርስቲያን ለመግባት ያለው አንድ በር ብቻ ነው። በበሯ ከተገባ በኋላ ግቢዋ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው። ይቺ ቦታ በትግራይ እንደ ደብረ ዳሞ፣ በበጌምድር እንደዙር አምባ፣ በመንዝ እንደ አፍቅራ ናት። እንደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ቤተክርስቲያኗ በየዘመኑ የተለያየ ስያሜን አግኝታለች። ከአጼ ድልነዐድ ዘመን (፰፻፷፮(866) ዓ.ም) እስከ ፲፩ኛው ክፍለ ዘመን በአሁኑ ስያሜ (ደብረ ከርቤ) ትታወቅ ነበር። በ፲፩ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ላሊበላ ከቋጥኝ ድንጋይ ፈልፍለው እግዚአብሔር አብ የተሰኘ ቤተክርስቲያን በዚሁ ቦታ ሲያሰሩ ደብረ እግዜአብሔር በሚል ስም ታወቀች። ከዚያም በዓጼ ድግናዣን ዘመን መንግሥት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ደብር ነጎድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ከደብረ እግዚአብሔር ደብረ ነጎድጓድ ተብላለች። ብዙ ሳይቆይ ግን ደብረ ነገሥት ተባለች።
በ፲፬፻፵፮(1446) አጼ ዘርአ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን በዚህ ስፍራ ሲያርፍ ደብረ ነገሥት መባሏ ቀርቶ ደብረ ከርቤ ተባለች። በዚህ ጊዜ የነበረው የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መምህረ እስራኤል ዘ ደብረ ከርቤ ይባል ነበር። አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው እየገሰገስገሱ ስለመጡ በግዕዙ ገሰ ወይም በአማርኛው ገሰገሰ የሚለው ቃል ለቦታው ስያሜ ሆነ። በዘመናት ሂደት ገስ ወደ ግሸን የሚለው ስያሜ ተዛወረ። አካባቢው በዚህ ስም ታወቀ።
በአቅራቢያዋም ከሚገኙ በርካታ ታሪካውያንና ጥንታውያን መካናት መካከልም፦
- ጥንታዊው የደብረ ሐይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ገዳም፣
- የድጓ ምስክር የነበረው ደብረ እግዚአብሔር፣
- የቅኔ ትምህርት ምንጭ የሆነው ዋድላ/ደላንታ፣
- የ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን የሃይማኖት ውሳኔ የተደረገበት የቦሩ ሜዳ ሥላሴ፣
- የውጫሌ ውል የተፈረመበት (ይስማ ነጉሥ) የውጫሌ ከተማ፣
- የመቅደላ አምባ፣
- የበሽሎ ወንዝ ሸለቆና ሌሎችም ናቸው።
በቅዱስ ላልይበላ ዘመን እንደተፈለፈሉ የሚነገርላቸው ጅምር ዋሻዎች አሁንም በደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ይገኛሉ። ደብረ ከርቤ የነገሥታት መናኸሪያ የሊቃውንት መገኛ የቤተክርስቲያን የሐዲስ ኪዳን ሥርዓት መፈጸሚያ ቅድስት ቦታ ነበረች። በመጨረሻም በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል መቀመጫ ሆናለች። ይቺ ድንቅ ተአምር የተገለጠባትና የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ክፋይ የሚገኝባት ጥንታዊቷ ግሸን ደብረ ከርቤ ከ፲፬፻፵፱(1449)ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ መስከረም ፳፩ የንግሥ በዓሏ ይከበራል።
ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም፤ ለብዙ ዘመናት፤ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ነገሥታት የሚጎበኙዋትና ልጆቻቸውንም እውቀት እንዲቀስሙ የሚልኩባት ስፍራም ነበረች። ለእመ አምላክ ዓመታዊ ንግሧ በዛሬዋ እለት እልፍ አእላፍ ምእመናን በስፍራው ለበረከት የሚገኙበት ክብረ በዓል፤ ጉዞው በአቀበት መንገድ ላይ በመሆኑ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጓዝ ሰው፤ የዛሬን ልመለስ እንጂ ሁለተኛ አልመጣም ሊል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ገና ቁልቁለቱን ወርዶ እናትና ልጅ ወዲያና ወዲህ ፈንጠር ብለው በቆሙበት ድንገት መሀላቸውን ገምሶ ባለፈ ደራሽ ውኃ ተለያይተው ቀሩ የሚባልባት ተለያየን ወንዝን እልፍ ሲል፤ በከፍተኛ ጉጉት ለቀጣዩም ዓመት ስለመሄድ መመኘቱ አይቀርም። የግሸን መንገድና የሴት ልጅ ምጥ አንድ ነው ይባላል ከነተረቱም፡፡
ፍጽመነ ንዕትብ በዕፀ መስቀሉ፤
ነግሀ ነቂሐነ እምንዋም በከመ ይቤሉ አዕማደ ሰላም፤
ዘዮም መስቀል አሠነየ ዓለመ እንተ በልየ፤
በስነ ማርያም አዋከየ፤
ለክርስቲያን ኮኖሙ ዕበየ።
የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም የግማደ መስቀሉ፣ የአባቶቻችን ሊቃውንትና ነገሥታት በረከት አይለየን።
መልካም በዓል ይሁንላችሁ!!
አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል
የአማራ ትስስር በቻይና
መስከረም 21 2015 ዓ.ም
ቻይና