ይህ የአማራ ትሥሥርር በቻይና ይፋዊ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ድረ-ገጽ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ልማድ፣ አርበኝነት፣ ቅርስ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችንም ጭምር ለአባላት በሚገባ እናሳውቃለን። የድረ-ገጹ ዋና አላማ የአማራን ታሪክ በሚገባ ለሁሉም በማስተማር ታሪካችንን ወደቀደመ ልዕልናው መመለስ ነው። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤ አንዲት ነጻ ሃገር ኢትዮጵያ -->

ደመራ እና የመስቀል በዓል ታሪኩ እና አከባበሩ

የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚብሔር ኃይል ነው። (ቆሮ ፲፰)


እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ!!

የዓለም መድኃኒት ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ በምቀኝነት ሰቅለው ገደሉት፤ ከገደሉት በኋላም ሕግ መተላለፋቸውን እና አንዳች በደል ያልተገኘበትን ጌታ በመግደላቸው ሕግ ተላልፈው ጻድቁን ገደሉት ይሉናል በማለት እና የመስቀሉን ተአምራት በማየት ክርስቲያኖች እንዳይድኑበት መስቀሉን ጉድጓድ ቆፍረው እንደቀበሩት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳናል። ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም በደል ሳይኖርበት ዓለምን ለማዳን እና የሰውን ልጅ ሁሉ ከኃጢአት እና ከበደል ነጻ ለማድረግ ሲል እንደ በደለኛ ከአመፀኞች ጋራ ተቆጥሮ አይሁድ በግፍ በሰቀሉት ጊዜ ክቡር አካሉ ያረፈበት እጅ እና እግሩ በችንካር የተቸነከሩበት ጎኑ በጦር ተወግቶ ደሙ የፈሰሰበት በመሆኑ ከዕፅዋት ሁሉ የላቀ ክብር እና ሞገስ ያለው ቅዱስ ነው። መስቀል የክብር ባለቤት መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በክቡር ደሙ ያከበረው፥ በቅዱስ ሥጋው የቀደሰው እንዲሁም መለኮታዊ ኃይሉ እና ባሕርያዊ ሕይወቱ  ያረፈበት ስለሆነ ኃይልን፣ ሕይወትን፣ ፈውስን እና ጽናትን የሚሰጥ ሆኖ በገቢረ ተአምርነቱ እየተገለጸ እና እየታወቀ በመሄዱ መስቀል የእግዚአብሔር ኃይል እና ጥበብ መገለጫ ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው እና ከዕረገቱ በኋላ ድውያንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሳት፣ እንካሶችንና እውራንን በማዳን ተአምራቱንና ኃይሉን መግለጽ የጀመረው በቅዱስ መስቀሉ ነው። ከዚህም የተነሳ እኛ ያመነው  እና ድንቅ ተአምራቱን የተመለከትነው ሁሉ ሕይወት እና ቤዛ የመሆን ጸጋ የተሰጠው መሆኑን ስለምናውቅ መስቀል ኃይላችን መስቀል ቤዛችን መስቀል የነፍሳችን መድኃኒት ነው እያልን የጸጋ እና የአክብሮት ስግደት እንሰግድለታለን።

የመስቀል ነገር በመጀመሪያ የተገለጸው በመላእክት ዓለም ነበር። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሥነ ፍጥረትን በጻፈበት አክሲማሮስ በተባለ መጽሐፉ እግዚአብሔር መላእክትን ፈጥሮ በተሰወረባቸው ጊዜ ዲያብሎስ እኔ ፈጠርኳችሁ አለ። ያን ጊዜ በመላእክት ዓለም ረብሻ ሆነ፤ ከፊሉ ዲያብሎስን አምኖ ከእርሱ ጋር ሆነ፤ ቅዱስ ገብርኤል ግን የፈጠረንን እስክናገኝ በያለንበት ጸንተን እንቆይ አለ፤ ቅዱስ ሚካኤልና ሌሎች መላእክትም አብረው ጸንተው ቆዩ፤ ተጠራጥውም ከሁለቱም ጎን ሳይሆኑ የቀሩ ነበሩ። ከዚያም በመላእክትና በዲያብሎስ መካከል ጦርነት ተጀመረ፤ በተዋጉ ጊዜ ዲያብሎስ ሁለት ጊዜ አሸነፋቸው፤ ሆኖም መላእክት አምላካቸውን ፈቃድህ ነውን? ብለው ቢጠይቁት፤ ፈቃዴስ አይደለም፤ ድል የምታደርጉበትን ኃይል እንድታውቁት ብዬ ነው እንጂ ብሎ በክንፋቸው ላይ የብርሃን መስቀል ቀረጸላቸው፤ በእጃቸው ደግሞ የብርሃን መስቀል አስያዛቸው፤ ሔደውም ዲያብሎስን ቢገጥሙት በመስቀሉ ኃይል ድል ነስተውታል። መላእክት ሳጥናኤልን ድል ያደረጉት በመስቀል ኃይል ነው (ራዕ. ፲፪፥፯ እና መዝ. ፶፱፥፬ ላይ መመልከት ይቻላል)

መስቀል በዘመነ አበው

በዘመነ አበው መስቀል የመባረኪያ ምልክት እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል። ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች በእምነት ባረካቸው ወአስተሐለፈ እዴሁ ላዕለ ርዕሰ ኤፍሬም ወምናሴ፤ እጆቹን በኤፍሬምና በምናሴ ላይ በመስቀል ምልክት አድርጎ ጭኖ ባረካቸው ይላል። (ዘፍ. ፵፰፥፲፩)፤ ዕብ. ፲፩፥፳፪)

ዛሬም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህኑ ቀድሶ በሚወጣበት ጊዜ በእጆቹ ይባርካል፤ ይህም የሚያሳየው ቤተ ክርስቲያኗ መሠረቷ ከላይ በዓለመ መላእክት ከታች ደግሞ በዘመነ አበው ያየነው መስቀል መሆኑን ነው።

መስቀል በብሉይ ኪዳን

መስቀል በብሉይ ኪዳን እንደየሀገሩ ሁኔታ ልዩ ልዩ ተግባራት ሲፈጸምበት ቆይቷል። ለምሳሌ:-

. ለወንጀለኞች መቅጫነት አገልግሏል

የየሀገሩ መቅጫ የተለያየ ነው።

                💫የጽርዓውያን ሰይፍ፣

                💫 የባቢሎን ዕቶነ (እሳት) እና ግበ አናብስት፣

                💫 የአይሁድ ውግረተ አዕባን (ድንጋይ)፣ 

                💫የፋርስ እና የሮም ስቅላት ነው።

ሰዎችን ሰቅሎ መግደል የተጀመረው በፋርስ ነው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰቀለውም ሐማ ነው (መ.አስ. ፯፥፱)። ሮማውያን ከእነርሱ ወስደው እንደተገበሩት ይነገራል፤ አይሁድም ብዙ ጊዜ ወንጀለኞችን የሚቀጡት በውግራት በእሳት ማቃጠል ቢሆንም በመስቀልም ነበር። ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች አይገረፉም፤ በመስቀል ይቀጡ ነበር። ከተገረፉ ደግሞ አይሰቀሉም። (ዘዳ. ፳፩፥፳፩-፳፫) በጌታ ላይ ግን ከሕጋቸው ውጭ ግፍ ፈጽመውበታልገርፈውም ሰቅለውታል።

፪. ለአርማ ይጠቀሙበት ነበር

የኢትዮጵያ ነገሥታትን ጨምሮ የሌሎች ሀገር ነገሥታትም እንደ አርማ ይጠቀሙበት ነበር። በእጃቸውም ይይዙት፣ በጦርነት ጊዜም በዘንግ አምሳል እንደሚይዙትና በፈረሶቻቸው ግንባር ላይ ይሥሉት እንደነበር ይገለጻል።በአጠቃላይ በብሉይ ኪዳን መስቀል በብዙ ኅብር/ምሳሌ ተገልጧል። ለምሳሌ፦ ሙሴ የኤርትራን ባሕር የከፈለባት በትረ ሙሴ ይባላል(ዘጸ. ፲፬፥፲፮)። የሙሴ በትር ባሕር ከፍሏል፣ ጠላት አስጥሟል፣ መና አውርዷል፣ ደመና ጋርዷል፣ ውሃ ከዐለት አፍልቋል፣ በግብፃውያን ላይ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል። ሙሴም ምሳሌው የሆነለት ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀልም ባሕረ እሳትን ከፍሏል፣ ማየ ገቦን ደመ ገቦን ለመጠጣችን ለጥምቀታችን አስገኝቷል። ኃይሉን በዲያብሎስና በአጋንንት ላይ አሳይቷል፣ ነፍሳትን ከሲዖል ባርነት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነጻ አውጥቷል። 

መስቀል በሐዲስ ኪዳን      

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ፣ ሰው ሆኖ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ድኅነትን ለሰው ልጆች ሰጥቶ፣ በመስቀሉ ተጣልተው የነበሩ ሰባቱን መስተፃርራን (ሰውእግዚአብሔርን መላእክትሰውንነፍስሥጋን፣ ሕዝብአሕዛብን) አስታርቋል። መስቀል በሐዲስ ኪዳን የመዳን ምልክት መሆኑ የተረጋገጠበት በክርስቶስ ደም የተቀደሰ፣ የጠብ ግድግዳን ያፈረሰ፣ ቅድስናና ክብር ያለው የአበው ተስፋ የተፈጸመበት፣ ሰው ከውድቀቱ የተነሳበት መሆኑ ተረጋግጧል። ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር  እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ (መዝ. ፸፫፥፲፪) መድኃኒት መስቀል መድኃኒት ክርስቶስን ተሸክሞ ታየ (ዮሐ. ፲፱፥፲፯፣ኤፌ. ፪፥፲፮፣ ቆላ. ፩፥፳)።

ደመራ

ደመራ የሚለው ቃል ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወሰደ ሲሆን  መጨመር፣መሰብሰብ፣መከመር፣ መቀላቀል፣መጣመር፣ መገናኘት እንዲሁም መዋሐድ እንደ ማለት ነው። ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ደመራ የሚለውን ቃል ደመረ ከሚለው የግእዝ ቃል አውጥተው ደመራ ግእዝና አማርኛን ያስተባበረ መሆኑን ገልጸው የበዓለ መስቀል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታ የደመራ እንጨት የሚደምሩበት በዓል ነው። ቤተክርስቲያናችንም ከምታከብራቸው ዘጠኙ የጌታ ንዑሳን በዓላት ውስጥ አንዱ ነው።

የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ከቁስጥንጥንያ ተነሥታ ከጌታችን መድኃኒችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች። ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ የጌታችን መስቀል ተአምራትን እንዳያደርግ አይሁድ በምቀኝነት ቀብረውት ነበርና የተቀበረበትን ቦታ የሚያሳያት አጥታ በመፈለግ ብዙ ጊዜ አሳለፈች። በኋላ ግን አንድ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊ አካባቢውን እንዲህ ሲል ነግሯት ነበር። ከሦስቱ ተራሮች በአንዱ ነው ያለው ይባላል።  በኋላክ ሱባኤ ገብታ ስትጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ ዕሌኒ ዕሌኒ ብሎ ጠርቶ በራዕይ ነግሯታል። ከዚያም በኋላ ደመራ አስደምራ ዕጣን አጢሳ ወደ ፈጣሪዋ ብትማፀን የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ መንበረ ጸባዖት ደርሶ ተመልሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ስፍራ አመለከታት። እርሷም በምልክቱ መሠረት ብታስቆፍር የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር መስቀል አገኘች፤ ከእርሱ መስቀል ጋር ሁለት ወንበዴዎች የተሰቀሉበትን መስቀል አብራ አግኝታው ስለነበር የጌታችን መስቀል ለይታ ያወቀችበት መንገድ ግን ድውያንን በመፈወሱ፣ አንካሳ በማበርታቱ፣ ጎባጣን በማቅናቱ የዕውራንንም ዐይን በማብራቱ ነው። ስለዚህም በየዓመቱ የመስቀልን በዓል ስናከብር ደመራ የምንደምረውና የምናበራው ንግሥት ዕሌኒን አብነት በማድረግ ነው። እርስዋም መስከረም ፲፯ ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት ፲ ቀን መስቀሉን አግኝታ አስወጥታ የቤተ ክርስቲያኑም መሠረት ወዲያው እንዲጣል አደረገች፤ የደመራ ሥርዓት ከዚህ ሲያያዝ የመጣ ነው። መስቀሉ ከተገኘ በኋላ በዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ከመስቀሉ በረከትን ማግኘት ጀመሩ። ይህንን የተመለከቱ በመስቀሉ ያላመኑ ሰዎች( ፋርሶች) ክርስቲያኖች እንዳይድኑበት እንደ ቀድሞው እንደ አይሁድ ኢየሩሳሌምን ወርረው መቅደሱን ሰብረው መስቀሉን ሰብረው ወሰዱት። ከዚያ በኋላ የቤዛንታይን ንጉሥ የነበረው ሕርቃል ምእመናንን በጸሎት ጠይቆ ወደ ፋርስ በመዝመት ድል አድርጎ መስቀሉን ይዞ ተመለሰ። ቅዱስ መስቀሉም ፯፻፲፬ ዓመታት በኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ወደ ግሪክ ወስደው የዓለም ክርስቲያን ነገስታት ለበረከት ተካፍለውታል። የጌታችን ቀኝ እጅ ያረፈበት ለአፍሪካ ደረሰ። ከአፍሪካ ደግሞ ለግብጽ ደርሶ ነበር። 

 

ግማደ መስቀሉ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዴት መጣ?

የጌታ መስቀል ለብዙ ዓመታት በኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት መስቀሉን ለመውሰድ ጠብ ፈጠሩ። በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣የእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት። ከዚያም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ለዐራት ከፍለው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎች ታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የጌታችን የመድኃኒታችን የቀኝ እጅ ያረፈበት የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅድሳት ጋር በግብፅ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡

በኢትዮጵያ አጼ ዳዊት በነገሠ ዘመን ግብጻዊያን በክርስቲያኖች ላይ ሰልጥነው ግብጽ ሀገር አፍሪንጅ ትብሎ በሚጠራው ቦታ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችን ጨፈጨፏቸው። አጼ ዳዊትም ጭፍጨፋው ካላቆመ ወደ ግብጽ ወታደሮችን እንደሚያዘምት እና የዓባይንም ወንዝ እንደሚገድብባቸው ትእዛዝ አስተላለፈ። በዚህ ጊዜ የግብጽ መንግሥት ዲፕሎማቶቹን የወርቅ፣ የብር እና የዝሆን ጥርስ እንዲሁም ሌሎች የከበሩ ገጸ በረከቶችን በማስያዝ አጼ ዳዊትን እንዲማፀኑ ላኳቸው። ኢትዮጵያዊው ንጉሥ አጼ ዳዊት የግብፅ ክርስቲያኖች በአማሌቃውያን ከሚደርስባቸው ተጽዕኖ ነጻ እንዲወጡ በማድረጋቸው የግብፅ ፓትርያርክ የከበሩ ስጦታዎችን ላኩላቸው። ንጉሡ አጼ ዳዊት ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው ወርቅ ሳይሆን ጌታ የተሰቀለበትን መስቀሉን እና ቅዱስ ሉቃስ የሳላትን ምስለ ፍቁር ወልዳ ስዕል አድኅኖ እንደሚፈልጉ ነግረው መለሷቸው። በመሆኑም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግማደ መስቀሉን፣ ምስለ ፍቁር ወልዳ ስዕል እንዲሁም ሌሎች ንዋየ ቅድሳትን አድርጋ ለኢትዮጵያ ሰጥታለች።

እሳቸውም በሱዳን እና በኢትዮጵያ ድንበር ልዩ ስሙ ስናር ከሚባለው አካባቢ ሲደርሱ መንገድ ላይ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። ልጃቸው አጼ ዘርያዕቆብም መስቀሉን አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል በተባሉት መሰረት በዳግማዊት ጎልጎታ በግሸን ደብረ ከርቤ አስቀምጠውታል። ይህ ግማደ መስቀል በግሸን ማርያም ገዳም በእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ ኢትዮጵያን እየባረከ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መስቀልን ከሐዋርያት በተማረችው መሠረት የወርና የዓመት በዓል ሠርታ ታከብረዋለች። መስከረም ፲፮ ቀን ደመራ ደምራ ጸሎትና ምሥጋና ታቀርባለች። ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት መሬት በእሌኒ አማካኝነት መገኘቱን ስታስብ በአሁኑ ዘመን ከብዙ ሰዎች ልቡና የተሠወረው መስቀል እንዲገለጥላቸው ትጸልያለች:: በመስቀል የሚገኘውን በረከት እየተቀበለች በመስቀል የሚመሰለውን መከራ ሁሉ ትታገሣለች:: መስቀል በካህናት በምእመናንና በምእመናት ልቡና ተስሏል:: በአንገታቸውና ልብሳቸውም መስቀል አለ:: ሥራ ሲጀመርና ምግብ ሲቀርብ በመስቀል አምሳያ ይማተባል:: መስቀል ለሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ  ነው:: “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ 16፡24) እንዳለ ጌታችን ቤተ ክርስቲያናችን ዕለት ዕለት መስቀሉን ትሸከማለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ መስከረም ፲፮ ቀን የምትደምረው ደመራ አገራዊ አንደምታም አለው። የመስቀል ደመራ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እውቅና ተሰጥቶት ዓለም አቀፋዊ ቅርስ ተብሎ ተመዝግቧል።

በአጠቃላይ ከዚህ ዕለት ምን እንማራለን፦ 

፩. በመስቀሉ ድነናል(በእርሱም እንደቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፤ ኃጢያታችንም ተሰረየልን። ኤፌ  ፩፥)

፪. በመስቀሉ ክርስቶስ ወደራሱ  አቅርቦናል(እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ካልሁ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ ዮሐ ፲፪፥፴፪)

፫. በመስቀሉ ሰላምን አግኝተናል(ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ባፈሰሰው ደም ሰላምን አደረገ ቆላ ፩፥)

፬. በመስቀሉ የእዳ ደብዳቤያችን ተደምስሷል( ከባላጋራችን የተነሣ በትእዛዝ የእዳችንን ደብዳቤ ደመሰሰልን፤ ከመካከላችንም አራቀው፤ በመስቀሉም ቸነከረው ቆላ ፪፥፲፬ )

፭. በመስቀሉ ላይ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ሞገስን አግኝተናል( እንግዲህ ወንድሞች ሆይ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ወደ መቅደስ ለመግባት ባለሙአልነት አለን ዕብ ፲፥፲፱)

፮. የተሰቀለውን ክርስቶስን መስበክ እንዳለብን ተረድተናል( እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ስንፍና ነው ፩ቆሮ ፩፥፳፫ )

፯. ስለ እኛ በመስቀል መከራ የተቀበለውን የክርስቶስን ፍለጋ መከተል እንዳለብን ተምረናል( ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደል ታውቃላችሁ። ነውር እና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ደም ነው እንጂ። ዓለም ሳይፈጠር የታወቀ በኋላ ዘመን ስለ እናንተ የተገለጠ ከሙታን ለይቶ ባስነሳው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ቃል ያመናችሁ አሁንም እምነታችሁ እና ተስፋችሁ በእግዚአብሔት ይሁን ፩ጴጥ ፩፥ ፲፰-፳፩)

፰. በመስቀሉ ላይ ለድኅነት የፈሰሰውን ቅዱስ ምስጢር በእምነት መቀበል ይኖርብናል( ደቀ መዛሙርቱ  ሲበሉ ጌታችን ኢየሱስ ኅብስቱን አንስቶ ባርኮ ቆርሶም ይህ ሥጋዬ ነው፤ እንኩ ብሉ ብሎ ሰጣቸው። ጽዋዉንም አንስቶ አመስግኖ እንኩ ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ ብሎ ሰጣቸው ማር ፲፬፥፳፪ -፳፫)

፱. በመስቀሉ በፈሰሰው ደሙ ጽድቅን፣ ቅድስናን እና ቤዛነትን አግኝተናል( በፈቃዱም አንድ ጊዜ በተደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋው ቁርባን ተቀደስን ዕብ ፲፥፲ ፤ እናንተም በኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ናቸሁ፤ በእርሱም ከእግዚብሔር ጥበብን፣ ቅድስናን እና ቤዛነትን አገኘን ፩ቆሮ ፩፥  )

፲. መስቀል ኃይልችን እና መመኪያችን እንደሆነ ተረድተናል።

ከሀገር ቤት ርቀን የምንገኝ ኢትዮጵያውያንም የበዓሉን ታላቅነት ለጓደኞቻችን እና ለምንኖርበት ኅብረተሰብ ማስረዳትና የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆኑ ማድረግም ይጠበቅብናል።  

የደመራ በዓልአከባበር 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር !!                            

 

አዘጋጅ፦ የባሕል ክፍል 


የአማራ ትስስር በቻይና

መስከረም  16   2015 ዓ.ም 

ቻይና


የአማራ ትስስር በቻይና(ANiC)

የአማራ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ፣ ሃይማኖትና ባህል ያለው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት የሆነ፤ ሃገር የሰራ፣ ነጻነቱን ያስጠበቀ፤ የራሱ የሆነ ፊደል ያለው፤ የጥንታዊ ትምህርት ስርዓት ባለቤት የሆነ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ በሃገረ መንግስት ምስረታ ሃገርን ከወራሪ መጠበቅና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ታላቅ ገድል በመስራት እኛ ልጆቹ ቀና ብለን እንድንሄድ አድርጎናል።

Post a Comment

ቀዳሚ ገጽ ተከታይ ገጽ
hi