አጼ ፋሲለደስ
አፄ ፋሲል የአፄ ሱስንዮስና የደብረታቦር ቆማ ፋሲለደስ ተወላጇ ወይዘሮ ወልደሰዓላ ልጅ ናቸው በልጅነታቸው በጣና ሐይቅ ላይ ባሉ ገዳማት መንፈሳዊና ዓለማዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በቆይታቸውም ስለመንግሥት አወቃቀር፣ ስለፍርድ አሰጣጥና ስለሕዝብ አስተዳደር እንዲሁም ስለሌሎች ጉዳዮች በሚገባ አጥንተዋል።
በ፲፮፻፳፬ ዓ.ም ዓለም ሰገድ(ዓለም የሰገደልህ) በሚል ስመ መንግሥት በአባታቸው ዙፋን ተቀመጡ። አጼ ፋሲል በአባታቸው እግር ተተክተው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሀገሪቱ ከፍተኛ መረበሽ ውስጥ ነበረች። አጼ ፋሲልም የመጀመሪያውን የሥልጣን እርምጃቸውን ያደረጉት የሀገሪቱ መረበሽ ምክንያት የነበረውን የካቶሊክ እምነት ብሔራዊ ሃይማኖት መሆንን ተዋሕዶ ይመለስ፤ የሮም ሃይማኖት ይፍለስ በማለት ወደ ኦርቶዶክስ በመመለስ ሀገሪቱን ማረጋጋት ነበር። ወዲያውም በማከታተል ከግብፅ አገር አዲስ ጳጳስ እንዲላክለት በማድረግ በአባቱ ዘመን እንዲደበዝዝ ተደርጎ የነበረውን የግብፅና ኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት እንዲጸና አደረገ። በኬኒያ የሚገኘው የሞምባሳ ወደብ በፖርቱጋሎች መደብደቡን ሲሰማ፣ የሮማው ፓፓ ከበስትጀርባው ያለበት ሴራ ነው በማለት በምድሩ የነበሩትን የካቶሊክ ጀስዊቶች በመሰብሰብ አባረራቸው።
ንጉሡም ፋሲል ይንገሥ፤ተዋሕዶ ይመለስ፤የሮም ሃይማኖት ይፍለስ በተባለው መሰረት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን ስላደረጉ ሕዝቡ፣ የቤተ ክህነቱና የቤተ-መንግሥቱ ሰው ሁሉ ንግሥናቸውን በደስታ ተቀበለው። ለዚህ ተግባራቸውም ሕዝቡ እንዲህ ሲል በግጥም መርቋቸዋል…
አጤ ፋሲል ተነገሱ
ሃይማኖትን አስመለሱ፣
በሰማይ ቤት ወርቅ ይልበሱ።
የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነ ሰው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባም አዘዙ፤ የካቶሊክ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን ላይ ታች ብሎ አፄ ሱስንዮስን ያሳመናቸው አልፎንሶ ሜንዴዝ የተባለ የካቶሊክ ቄስና አውሮፓውያን ደቀ መዛሙርቱ ከኢትዮጵያ ምድር እንዲባረሩ ተደረገ።
አፄ ፋሲል በነገሡ በሦስተኛው ዓመት መልዓከ ክርስቶስ የተባለ የላስታ ባላባት የዙፋን ተቀናቃኝ ሆኖ ተነሳባቸውና ጥቂት ተዋግተው ንጉሡ ለጊዜው ተሸንፈው ሲሸሹ የላስታው ባላባት ቤተ-መንግሥት ገብተው በአፄ ፋሲል ዙፋን ተቀመጡ። አፄ ፋሲልም ወዲያውኑ የስሜን፣ የዳሞትንና የበጌምድር አገረ ገዢዎችን ከጎናቸው አሰልፈው ከመልዐከ ክርስቶስ ጋር ተዋጉና አሸንፈው ወደዙፋናቸው ተመለሱ።
ከዚያ በኋላም ሀገሩ ሁሉ ሰላም ሆነ። ንጉሱም ከአስተዳደር ስራቸው በተጨማሪ፣ እንደምትመሰረትና የመንግሥት መቀመጫ እንደምትሆን ለረጅም ዘመናት ትንቢት ሲነገርላት የነበረችውን የጎንደር ከተማን መስርተው የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አደረጓት። የጎንደር አመሰራረት ልዩ የሆነ ኃይማታዊ ምስጢር እንዳለው በታሪክ ድርሳናት ተፅፏል። አከታትሎም የፋሲል ግቢንና ፵፬ቱ ታቦታት ተብለው የሚታወቁትን የጎንደር ከተማ አብያተ ክርስቲያናት መሰረት ጣለ። በአፄ ፋሲል ከተመሰረቱት ታዋቂወቹ ፵፬ አብያተ ክርስቲያናት፣ ታዋቂወቹ አደባባይ ኢየሱስ፣ አደባባይ ተክለ ሃይማኖት፣ አጣጣሚ ሚካኤል፣ ግምጃቤት ማርያም፣ ፊት ሚካኤል፣ እና ፊት አቦ ይገኙበታል። ያለመታከትም ፯ የድንጋይ ድልድዮችን በማሰራት እስካሁን ድረስ ስሙ ሲጠራ ይኖራል። አልፎም በግራኝ አህመድ ዘመን በእሳት ጋይቶ የነበረችውን አክሱም ጽዮን በአዲስ መሰረት እንደገና ማሰራት ችሏል።
በቀጣይም አጼ ፋሲል የተለያዩ ፈተናዎችንና አመጾችን እያለፉ የአስተዳደር ሁኔታቸውን በመልካም ሁኔታ ቀጠሉ። ጎንደርን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አድርገው መሰረቱ። በርካታ አብያተክርስቲያናትን አሳነጹ። በኪነ-ሕንጻ ጥበባቸው ወደር የማይገኝላቸውን የፋሲል ግንብንና ግቢን አሰሩ።
አፄ ፋሲል በዘመናቸው ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል በብዙ ወንዞች ላይ ያሰሯቸው ድልድዮች ይጠቀሱላቸዋል። ፲፪ ድልድዮችን እንዳሰሩም ይነገራል። ሕዝቡም እንዲህ ብሎ ገጥሞላቸዋል…
ርብ እና ዓባይ መንጠቅ የለመዱ፣
እንደልማዳቸው ሰውን እንዳይጎዱ፣
በፋሲል ዳኝነት ተፈጥመው ሄዱ።
ርብ እና ዓባይ ሸፍተው ሲኖሩ፣
አላፊ አግዳሚውን ከጎራ እያሰሩ፣
በትላልቅ ድንጋይ ተደብድበው ቀሩ።
ሕዝቡም በድልድዮቹ ላይ በተሻገረ ቁጥር የፋሲልን ነፍስ ይማር እያለ ይፀልይላቸው ነበር።
አፄ ፋሲል ከድንበራቸው አልፈው ከኢትዮጵያ በስተምዕራብ በኩል ያለውን የሱዳን ግዛት የሆነውን ስናርን ማስገበር የቻሉ ንጉሥም ነበሩ። በወቅቱም አዝማሪ እንዲህ ተቀኝቶላቸው ነበር…
ጎንደር ቢያጉረመርም ፋሲል ፈረስህ፣
ኑብያና ስናር ወርቁን ጫኑልህ፡፡
ሳሩን ተጠየፈ የፋሲል ፈረሱ፣
ክምር የሱዳን ወርቅ ገፈራው ነው ለሱ።
በሌላ በኩል አፄ ፋሲል በአባታቸው በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ከሮም መጥተው የነበሩ እህትማማቾችን አንዷን ውሽማ አንዷን ሚስት አድርገው በመያዛቸው ከካህናትና ከመነኮሳት ጋር የከረረ ፀብ ውስጥ ገብተው እንደነበርና አፄ ፋሲል ግን ከስህተታቸው ከመመለስ ይልቅ የሚቃወሟቸውን ሁሉ በብርቱ እንደቀጧቸው ታሪካቸው ያስረዳል። በኋላ ግን በስህተታቸው ተፀፅተው ይቅርታ እንደጠየቁና ምኅረት እንደለመኑ በታሪካቸው ተጽፏል።
ከኃያላን የጎንደር ነገሥታት መካከል አንዱ የነበሩት አፄ ፋሲል ጎንደርን መስርተውና የመንግስታቸው መቀመጫ አድርገው ፍርድ ሲሰጡ፣ ሀገር ሲያቀኑና ግዛት ሲያስፋፉ ቆይተው፣ መስከረም ፲፭ ቀን ፲፮፻፶፱ ዓ.ም፣ በነገሡ በ ፴፭ ዓመታቸው፤ በተወለዱ ደግሞ በ ፸፰ ዓመታቸው፣ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። አጼ ፋሲለደስ ካረፉ በኋል ብጥብት እንዳይነሳ በሚል ስጋት እረፍታቸው ተደብቆ በብላቴን ጌታ መልክዐ ክርስቶስ ትዕዛዝ የነጋሲ ዘሮች እንዲታሰሩ ተደረግ። ከዚያም ጥቅምት ፲ ቀን በዕለተ ማክሰኞ ማለዳ ላይ ዳግማዊ ደብረ ሊባኖስ ተብሎ በሚጠራው በአዘዞ ተክለሃይማኖት የቀብር ሥነስርዓታቸው ተፈጸመ። በኋላ ላይ አጽማቸው ከዚያ ወጥቶ በጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም በክብር ተቀመጠ።
መሉ ታሪኩን ለማንበብ ይህንን ሊንክ ይጫኑ።
አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል
የአማራ ትስስር በቻይና
መስከረም 15 2015 ዓ.ም
ቻይና