የሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ 90ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ
ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ ለመሆን ህልም የነበራቸው አፈወርቅ ይህን ህልማቸውን እውን ለማድረግ የመረጡት መንገድ የምዕራባውያን ጠበብትን የአሳሳል ዘይቤ መቅዳት ሳይሆን የራሳቸውን ዘይቤ መፍጠር ነበር። አፈወርቅ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በክብር ተገኝተው የከፈቷቸውን የኪነ-ጥበብ አውደ-ርዕዮችን ማሳየት የቻሉ ታላቅ ሰዓሊና ቀራፂ ነበሩ። በ1946 ዓ/ም በሀያ ሁለት ዓመታቸው የተለያዩ የስነ ጥበብ ሥራቸውን የሚያሳይ የመጀመሪያውን ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቅርበዋል። ከትርዒቱ ባገኙት ገቢ በድጋሚ ወደ አውሮፓ በመሄድ ለሁለት ዓመት በጣሊያን፣ በፈረንሳይ፣ በስፔን፣ በፖርቱጋል፣ በእንግሊዝና ግሪክ ጥልቅ የኪነ ጥበብ ጥናት አከናውነዋል። በጦርነትና በሌሎች ምክኒያቶች ተዘርፈው በነዚህ ሃገራት የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጥንታዊ የሃይማኖትና የታሪክ የብራና መጻሕፍትን በጥልቅ አጥንተውና የመስታወት ላይ ስዕል ( የሞዛይክ አሠራር ጥበብን ) ቀስመው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
ጎልተው ከሚታወቁት ሥራዎቻቸው መካከል የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው።
➥ ኪዳነ ምሕረት፣
➥ የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን የግድግዳ፣
➥ የመስኮትና የጣሪያ ስዕሎችና ሞዛይኮች፣
➥ እናት ኢትዮጵያ፣
➥ የመስቀል አበባ፣
➥ የዳግም ምፅዓት ፍርድ፣
➥ ደመራ፣
➥ በሐረር ከተማ የሚገኘውን የልዑል ራስ መኮንን ሀውልት፣
➥ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምስል፣
➥ የሐረር ጦር አካዳሚ ሥዕሎች፣
➥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የአፍሪካ አዳራሽ ስዕሎች፣
➥ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን የዘውድ ስርዓት እንዲሁም
➥ ንጉሥ ሰለሞን በኢየሩሳሌም ለንግሥተ ሳባ ያደረገላትን አቀባበል
አፈወርቅ ተክሌ ከፍ ያለ ችሎታና ስነ ምግባር ያላቸው አርቲስት ከመሆናቸውም ባሻገር በብዙ የሥዕል ሥራዎቻቸው ክፍለ ዓለማቸውን አጉልተው ስለገለፁና በኢትዮጵያ ስነ ጥበብን በዘመናዊ ቴክኒክ መሥራት ከጀመሩት ከቀዳሚዎቹ መካከል አንዱ ስለሆኑ በ1957 የመጀመሪያውን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ብሔራዊ የሥነ ጥበብ ሽልማት አሸንፈዋል። አፈወርቅ በበርካታ የዓለም ሀገራት ተዘዋውረው ብዙ የስነ ጥበብ ትዕይንቶችን አቅርበዋል። ከመቶ የማያንሱ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን እንዳገኙ የሚነገርላቸው አፈወርቅ ተክሌ የአራት ዓለም አቀፍ የሥነጥበብ አካዳሚዎች አባል ነበሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ የአገራቸው ስምና አጭር የሕይወት ታሪካቸው ተጽፎ ወደ ጨረቃ ከተላከላቸው 200 ታላላቅ የአገር መሪዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ደራስያን፣ ሠዓሊያን መካከል አንዱ አፈወርቅ ተክሌ ናቸው።
አፈወርቅ መኖሪያ ቤታቸውን እንዲሁም ስቱዲዮና ጋለሪ ያካተተውንና ቪላ አልፋ የተሰኘውን ሕንፃ ራሳቸው ዲዛይን ያደረጉት ሲሆን ስራውም 15 ዓመታት እንደፈጀ ይነገራል። 22 ክፍሎች ያሉት ቪላ አልፋ ጥንታዊቷን አክሱምን፣ የጎንደር ቤተ መንግስትንና የሐረር ግንብን በሚያንፀባርቅ መልኩ የታነፀ ነው።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ባደረባቸው ጽኑ ሕመም በሕክምና እየተረዱ ሳለ ማክሰኞ ዕለት ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም በተወለዱ በ79 ዓመታቸው በአዲስ አበባ ካዲስኮ ሆስፒታል አርፈዋል። የቀብር ስርዓታቸውም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
ምንጭ፦ ልዑል ዓምደጽዮን ሠርፀድንግል
አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል
የአማራ ትስስር በቻይና
ጥቅምት 13 2015 ዓ.ም
ቻይና
ሰናይ ውእቱ
ReplyDeleteThis comment has been removed by the author.
ReplyDelete