ዛሬ(ግንቦት 6) የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ 23ኛ ዓመት የሰማዕትነት መታሰቢያ እለት ነው።
ከቄስ ትምህርቱ ጎን ለጎን ድሬዳዋ ይገኝ ከነበረው ፈረንሳይ ሚሲዮን ገብቶ ቀለም መቁጠር ጀምሮም ነበር። የእናቱ አባት ቀኛዝማች ጽጌ ወረደወርቅ ታዋቂ አርበኛ ነበሩ። ቀኛዝማች ጽጌ ከሶስት ዓመት ተኩል እስር በኋላ ሐገራችን ነጻ ወጥታ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ አስራትን አዲስ አበባ አስመጥተው በ1934 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስገቡት። በትምህርት ላይ ጥሩ አቀባበል ሰለ ነበራቸው ከተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አጠቃላይ ተማሪዎች አንደኛ በመውጣት የካሜራ ተሸላሚ ነበሩ። በወቅቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ወጣቶች መካከል ላቅ ያለ ውጤት ያስመዘገቡትን ተማሪዎች ወደ ውጭ ሐገር ልኮ ማስተማር ተጀምሮ ነበርና አስራትም በዚሁ የትምህርት ዕድል ምክንያት ግብጽ ወደሚገኘው የእንግሊዞች ቪክቶሪያ ኮሌጅ ተላከ። በግብፅ አሌክሳንድርያ ቪክቶሪያ ኮሌጅ በ1946 ዓ.ም በቀዶ ጥገና ሙያ በጥሩ ነጥብ ተመርቀው ወጡ። ፕሮፌሰር አስራት ወደ ሌላ አገር ሳይሄዱ ህዝባቸውን ለማገልገል ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ለተከታታይ 5 ዓመታት ህዝቡን ሲያገለግሉ ቆይተው ወደ ስኮትላንድ ኤድንበርግ ዩኒቨርሲቲ የበለጠ ትምህርት ለመማር ሄደዋል። ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ሀገር ቤት ከረጅም ጊዜ ልፋት በኋላ የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የመጀመርያዉን የህክምና ትምህርት ቤት አቋቁመዋል። በሙያቸው መምህር፣ ሀኪምና የትምህርት ቤቱ ዲን ሆነው ደሀው ህዝባቸዉን አገልግለዋል።
በወቅቱ በተደጋጋሚ ወደ ዘመቻ የተላኩ ሲሆን፤ የሄዱበትን ዘመቻም በክብር ለመወጣት በቅተዋል። በዚህም መሠረት በ1968 ዓ.ም በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት በቃኘው ሆስፒታል፣ አስመራ፤ በ1969 ዓ.ም በድጋሚ በቃኘው ሆስፒታል፣ አስመራ፤ በ1970 ዓ.ም በራዛ ዘመቻ በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት እና ቡድን መሪነት በመቀሌ ሆስፒታል፤ እንዲሁም በሰኔ 1971 ዓ.ም በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት ምጽዋ ዘምተው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል። በህክምናው ዘርፍ አስራት የተባለ ጸበል ፈልቋል እስከመባል የደረሰ አንቱታን ያተረፉ ብቁ ሐኪም ነበሩ። ኢህአዴግ በብቃት ማነስ በሚል ከሌሎች 41 ምሁራን ጋር ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በ1985 ዓ.ም እስከሚያባርራቸው ድረስ ዩንቨርስቲውን በትጋት ያገለገሉ የሐገር ባለውለታ ነበሩ። በሙያቸው የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን፤ ጥቂቶቹን ለመዘርዘር ያክል
►የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የፈረሰኛ ደረጃ ፤
►የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን የፈረሰኛ ደረጃ ፤
►የአብዮታዊ ዘመቻ ዓርማ፤
►ዓለም አቀፍ የወርቅ ሜርኩሪ (በግል አስተዋጽኦ)፤
►የቀይ ባህር ኒሻን አንደኛ ደረጃ ይገኙበታል።
ምንም እንኳ አስራት ከደርግ ጋር ሆድና ጀርባ ሆነው የቆዩ ቢሆንም ህወሀት አዲስ አበባን በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም ሲቆጣጠር እፎይታ፣ አዲስ ዘመን፣ ማለዳ እና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተባሉት ጋዜጦችን በመጠቀም ከደርግ ጋር ወግነው እንደወጉት ስም ማጥፋት ጀመረ። ፕሮፌሰር አስራት ስለ ተባለው ጉዳይ ሲጠየቁ ግን "እኔ የህዝብ ልጅ ነኝ፤ በሙያዬ ከንጉሡ እስከ መንግሥቱ ቤተሰቦች፣ ከድሀ ገበሬው እስከ ወታደር፤ የሙያዉን ስነምግባር በሚጠብቅ ሁኔታ አገልግያለሁ። እነሱ እንደሚሉት ሳይሆን ምፅዋ ላይ የኢትዮጵያ ወታደር ወይም የተገንጣይ ሳንል አክመናል። አሁንም ቢሆን እርዳታዬ ካስፈለጋቸው ለማገልገል ዝግጁ ነኝ"ነበር ያሉት።
እኚህ ፕሮፌሰር ለየት የሚያደርጋቸው ስብእና በሙያው እንዳሉ ሌሎች አጋሮቻቸው የራሳቸው የግል ህክምና ተቋም ገንብተው ገንዘብ ለመሰብሰብ አንድም ቀን ያልሞከሩ ይልቅም ሕይወታቸውን በሙሉ ለሕዝብ ችግር አሳልፈው የሰጡ መሆናቸው ነው። ወደ አማራው ፖለቲካ ያስገባቸውም ይሄው ስብእናቸው ነበር። በሰኔ መጨረሻ 1983 ዓ.ም በአውሮፓውያን እና አሜሪካ አቀናባሪነት የተደረገው የብሄራዊ ሰላም ጉባኤ ላይ ፕሮፌሰሩ የከፍተኛ ትምህርት ትቋማትን ወክሎ የታደመው ቡድን አባል ሆነው ተሰብስበው ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የተለያዩ ብሄሮች የወከሉ ቡድኖች ሲኖሩ በህዝብ ብዛቱ ትልቅ የሆነው አማራ አልተወከለም ነበር። የስብሰባው ዋነኛ አጀንዳ ስለ ተጨቆኑ ብሄር ብሄረሰቦች ሲሆን ጨቋኝ ሆኖ የቀረበው ብሄር አማራው ነበር። አገዛዙ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች አጋፋሪነት አማራው ደርግና የአፄው ስርዓት ላጠፋቸው ጥፋቶች ሁሉ እንደ ዋና ባለቤት ተደርጎ ተወሰደ ቋንቋው ቆሻሻ ቋንቋ ወይም እንደ ኦነግ አጠራር afan ajawa ተብሎ ይጠራ ጀመር። በግልፅም የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስተር ታምራት ላይኔ ሳይቀር ኤርትራ ሄዶ በአማራው ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ የሚል ሰንፋጭ ንግግር አድርጎ መጣ። ሳይውል ሳያድር ይሄ በሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳ ፍሬ አፍርቶ ወደ ተግባር ተለወጠ።
ይህንን የቃላት ጦርነት ወደ ተግባር ለመለወጥ ሁሉም ታጣቂ ሀይሎች ተንቀሳቅሰዋል። በኦነግ፣ በኦህዴድ፣ በኢህአደግ አማካኝነት በበደኖ 154 ሰው ጊራዋ፣ ኩርፋ ጨሌ፣ ለንጋ፣ ኬርሳ፣ ሶካ፣ ደደር፣ ሂርና፣ ቁኒ፣ መስላ፣ ጋሊቲ፣ ደባ የተባሉ አከባቢዎች ከ1000 ሰው ባላይ አርባ ጉጉ ላይ ከሞተው ውጭ ከ32,000 በላይ አማራ ከመኖራያው ተፈናቅሏል። አርሲ ነገሌ 60 ሰው ወለጋ ከ200 አማሮች በላይ እንደ ዱር እንስሳ ታድነው ተገድለዋል። ይህ ከብዙ በጥቂቱ ነው። ሴቶችን መድፈር ፅንሳቸዉን በጩቤ እያወጡ ማሳየት ዋና ስብእና የጎደላቸው ድርጊቶች መፈፀም መደበኛ ድርጊቶች ነበሩ። ይህ ሁሉ ሲሆን ህወሀት ዳር ቆሞ ለኦነግ እና ሌሎች መሳርያ እያስታጠቀ ያልታጠቁ ንፁሃን ገበሬ አማሮችን አስጨፈጨፈ ነበር። የሚገርመው በቀደመ ስሙ ኢህዴን የጥምቀት ስሙ ብአዴን የሚባለው ደደብ ድርጅት ይህ ሁሉ ጭፍጨፋ ሲካሄድ አንድም ተቃውሞ አላደረገም።
እንግዲህ ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች እና ሌሎችም ተጨምረው ነው ፕሮፌሰሩን መአሕድን(የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅትን) በጥር 1984 ዓ.ም ሊያቋቁም ያስቻለው። መአህድ ገና ከጅማሮው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ፅህፈት ቤት ከፍቶ በመንቀሳቀስ ተፅዕኖ ማድረግ ጀመረ። በታህሳስ ወር 1985 ዓ.ም ብቻ ከ40 በላይ የመአሕድ ማእከላዊ ኮሚቴ ታስረዋል ፕሮፌሰር አስራት ከአርባ አንዱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር በአቅም ማነስ በሚል ፖለቲካዊ ስም ማጥፋት ታርጋ በገነት ዘውዴ በሚመራው ትምህርት ሚኒስተር አማካኝነት ተባረዋል።
በ1986 ዓ.ም አስራት ደብረ ብርሀን ስብሰባ ላይ ባደርጉት ንግግር አማካኝነት ህወሀት መንግስትን በኃይል ለመገልበጥ አሲረዋል ሲል ሁለት ዓመት ተኩል እስራት ፈረደባቸው። እዛው እስር ላይ እያሉ በ1987 ዓ.ም እንደገና በሌላ ክስ ሶስት ዓመት ጨመረባቸው። ይህ ሁሉ የሚሆነው ከ65 ዓምት በላይ የነበሩ አዛዉንት ላይ ነበር። አስራት ከዚህ ዓመት በኋላ ግን ጤና አጡ በተከታታይም በሀኪሞች የውጭ ህክምና ያስፈልጋቸዋል ቢባልም አገዛዙ ሊቀበል አልፈለገም። በመጨረሻ ከተዳከሙ በኋላ በታህሳስ ወር 1991 ዓ.ም ወደ ውጭ ሄደው ከ5 ወር በኋላ ግንቦት 1991 ዓ.ም በፊላደልፊያ አሜሪካ አረፉ።
የፕሮፌሰሩ አስከሬን ታላላቅ እንግዶች፤ ቤተሰቦቻቸውና አድናቂቆቻቸው በተገኙበት ግንቦት 15 ቀን ወደ ኢትዮጵያ አሸኛኘት ተደርጎለት ከዋሽንግተን ዲሲ ጉዞ ጀመረ። ግንቦት 15 ቀን 1991 ዓ.ም የተነሳው የፕሮፌሰሩ አስከሬን ሮም አርፎ ግንቦት 17 ቀን 1991 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደረሰ። በስፍራው ሲጠባበቅ የነበረው ህዝብ አስከሬኑን በከፍተኛ አጀብ ለገሐር ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አደረሰው። በመኖሪያ ቤታቸውም ሌሊቱን ጸሎተ ፍትኃት ሲደረግ አድሮ በማግስቱ አስከሬናቸው በመሠረቱትና በኋላም በሞቱለት ድርጅታቸው፣ መአህድ ጽ/ቤት ጥቂት ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል አመራ። በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ፍትሃትና ጸሎት ከተደረገላቸው በኋላ ቅድስት ስላሴ እንዳይቀበሩ መንግስት በመከልከሉ ምክንያት ግንቦት 17 ቀን 1991 ዓ.ም በባለወልድ ቤተክርስቲያን እንዲያርፉ ተደረገ። ይኸው ላለፉት 18 ዓመታት በባለወልድ የቆየው አጽማቸው ዛሬ ወደሚገባው ቦታ ወደ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ሊዛወር ችሏል። ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የሁለት ወንዶች ልጆች አባትም ነበሩ።


ይህ ከስር ሊንኩ የተያያዘው ጋሻው መርሻ የጻፈው ነው። መጽሐፉን በማውረድ እንድናነበው ለማለት እንወዳለን።
ታሪክ ክፍሎች እናመሰግናለን። በርቱልን።
ReplyDelete