አምሐራ ሳይንት
1. መሐል ሳይንት ወረዳ እና 2. ሳይንት አጅባር ወረዳ ናቸው።
አምሐራ ሳይንት በአማራ ክልል እምብርት በመገኘቱ ደቡብ ወሎ እና ምስራቅ ጎጃም እንዲሁም ከበጌምድር ግዛት ደቡብ ጎንደር ያዋስኑታል። ጎንደር ስማዳ ወረዳ በበሽሎ ወንዝ፤ ጎጃም እነብሴ ሳር ምድር/ መርጡለ ማርያም ወረዳ በአባይ ወንዝ፤ ወሎ በመቅደላ፣ በተንታ እና ለጋምቦ ወረዳ እንዲሁም ደብረሲና እና ቦረና ወረዳዎች ያዋስኑታል። ከሸዋ ደግሞ በመርሃቤቴ በቅርብ ርቀት ላይም ይገኛል። አካባቢው በታሪክ የአማሮች መገኛ አማረኛ ቋንቋን የፈጠሩ ጠበብቶች ቅኔን የደረሱ ሊቃውንት ዜማን ያመለከቱ የዜማ ከያንያን የነበሩበት የአብርሃ ወአፅብሃ ቤተ መንግስት የሚገኝበት የአፄ ይኩኖ አምላክ የፍርድ አደባባይ የአፄ ገላዉዴዎስ መናገሻ የእነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሀገር ነች። ጀግኖች ራሶችና ፍታውራሪዎች የነበሩባት በጦር በጎራዴ ሀገርን፣ ታሪክን እና ቅርስን ሲጠብቁ የኖሩባት የአርበኞች ሀገር ነች። አምሐራ ሳይንት የሰሜን ኢትዮጵያ ማዕከል የነበረች ለሀገራችን ኢትዮጵያ ቁልፍ ቦታ ነበረች። ጎንደር በጌምድር ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ቤተ መንግስት ከሰሜን ኢትዮጵያ ከለቀቀ በኋላ ሀገራችን ኢትዮጵያም በዘመነ መሳፍንት ከተከፋፈለች በኋላ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ምድር አምሐራ ሳይንት ጎስቋላ ሆና አስተዋሽ አጥታ እናት የሌለው ልጅ መስላ በመከራና በሰቆቃ በጨለማ ውስጥ የምትኖር ቦታ እንደነበረች ታሪክ ያስረዳል። አምሐራ ሳይንት ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ እና ሸዋ የአራቱም ዞኖች የሚገናኙበት ብቸኛ ማዕከል ነች። ቦታው የዓለም አቀፍ የጥንተ ስልጣኔ መመዘኛ መስፈርቶች ተሟልተው የሚገኙበት ነው። ከነዚህም መካከል ለአብነት የሚከተሉትን እንመልከት፦
1. ሃይማኖት፦ የኦሪት መስዋዕት ይሰዋበት የነበረ በዘመነ ክርስትና የሐዲስ ኪዳን ማዕከል ሆኖ የቀጠለ ነው።
2. ቋንቋ ፦ አማርኛ ቋንቋ የተፈጠረበት ምድር ነው።
3. ዜማ ፦ የዘመነ ብሉይ የአምልኮ መፈፀሚያ ዜማ የነበረበት ፣ በዘመነ ሐዲስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የሰዓታት ዜማ የደረሱበት ቦታ ነው።
4. ፍልስፍና ፦ ዮሐንስ ገብላዊ ቅኔ ደርሶ ያመለከተበት ቦታ ነው።
5. ትምህርት ፦በጽሑፍ ቋንቋ የአብነት ትምህርት ይሰጥበት የነበረ ቦታ ነው።
6. የመንግሥት አስተዳደር ፦ እንደ ክብረ ነገስት ያለ የሥርዓተ መንግሥት መምሪያ ቦታና መዋቅር የነበረበት አስገራሚ ቦታ ነው።
7 . የሐይማኖት እና የፍልስፍና ፣ የኪነ ጥበብና የስነ ጥበብ ድርሰቶች ያሉበት ቦታ ነው።
8 . የግዕዝ፣ የአረማይክ፣ የአማርኛ ጽሑፎች በብራና እና በድንጋይ ላይ ታትመው የሚገኙበት ቦታ ነው።
9. የጥንት ዘመን የጦር መሳሪያዎች እና የግብርና መሳሪያዎች፣ የእንስሳት እርባታና የሰብል ማምረቻ ጥንታዊ መገልገያዎች የሚገኙበት ቦታ ነው።
10. ስነ ህንጻ ፦ ከክርስቶስ ልደት በፊት የጥንት የስነ ህንፃ አሻራዎች፣ የአምልኮ መሰዊያ ቦታዎች፣ ሌዋውያን በእስራኤል ይሰሯቸው የነበሩ የሰቀላ ቤት አምሳያዎች ያሉበት ቦታ ነው።
በጠቅላላ አምሐራ ሳይንት የጥንት ፐርሺያ፣ ቻይና፣ ግብፅ እና ግሪክ የመሳሰሉት በስልጣኔ የተለኩበት በአገራችን የአክሱም ስልጣኔ የተገለጠበት ሁሉ ሳይጓደል ተሟልቶ የሚገኝበት ግን እስከ ዛሬ ታሪኩ ተዳፍኖ የኖረ ስፍራ ነው።
ተድባበ ማርያም
አሥራ ሁለቱ የተድባበ ማርያም በሮች ዝርዝር
⇛ ፊት በር
⇛ የጌላት በር
⇛ የታንኳ በር
⇛ አምጣ ፈረሴን በር
⇛ ግራዢ በር
⇛ ገተም በር
⇛ አቅቻ በር
⇛ ፈረስ መጣያ በር
⇛ ቦካ በር
⇛ ጨረር በር
⇛ የጎድ በር
⇛ መርገጫ በር
በብሉይ ዘመን መስዋዕተ ኦሪት ከተሰዋባቸው መካከል አክሱም ጽዮን፣ ተድባበ ጽዮን (የዛሬዋ ተድባበ ማርያም)፣ መርጡ ለማርያም፣ ጣና ቂርቆስ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ቀዳማዊ ምኒሊክ ከአባቱ ከንጉሡ ከሰሎሞን መንግስት ተቀብሎ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ 4 መናብርት ጽዮን ይዞ እንደመጣ ታሪክ ይናገራል። እንደ ኦሪቱ ስርዓት መናብርቱን ሲያፀናም፦1. የአክሱም ጽዮን (ንቡረ እድ)
2. የተድባበ ማርያም (ፓትርያርክ)
3. የመርጡለ ማርያም (ርዕሰ ርኡሳን)
4. የጣና ቂርቆስ (ሊቀ ካህናት) ተብለው ተሰየሙ።
ከቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ እስከ ጃንሆይ ዘመነ መንግስት ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ንጉስ ቀብተው የሚያነግሱ እነዚህ አራቱ መናብርተ ጽዮን ነበሩ።
►የአክሱም ንቡረ ዕድ ማንኛውም ንጉሥ ሲነግሥ ከሥርዓተ ንግሥ በኋላ ዘውዱን በክብር ከራሱ ላይ ያቀዳጃል፡፡
►ተድባበ ማርያም ፓትርያርክ "ቅንት ሰይፈከ ኃያል ውስተ ሐገርከ በሥንከ ወበላሕይከ አርትዕ ተሰራህ ወንገሥ በትረ ጽድቅ ወበትረ መንግስትከ" ብሎ ሰይፈ መንግስቱን ለንጉሥ ያስታጥቀዋል። በትረ መንግስቱን ህለተ ወርቁን ጠላትህን በእጅህ ጭብጥ በእግርህ እርግጥ አድርገህ ግዛ ብሎ በቀኝ እጅ ያሲይዘዋል። በዚህ እውነተኛ ፍርድ ፍረድበት የእግዚአብሔርን ሕግ ጠብቅበት የተበላሸውን አድስበት የታደሰውን አጽናበት አመፀኞችን ቅጣበት ፍቃዶኞችን ሹምበት በዚህ ሁሉ አምላካችንን አገልግልበት ብሎ ይሾመዋል፡፡
► የመርጡለ ማርያም ርእስ ርኡሳን ልብስ መንግሥቱን ያለብሰዋል፡
►የጣና ቂርቆሱ ሊቀ ካህን… ቅብአ ንግሥናውን ይቀባል
ይህ ሁሉ ሥርዓት የሚደርሰው 40 ቀን ለሥርዓተ ንግሥ የተወሰነው ከብሉይና ከሐዲስ ኪዳን የተውጣጣው ጸሎትና መሥዋዕት ካረገ በኋላ ነው። በእነዚህ አራት መናብርተ ጽዮን ያልነገሠ ንጉሥ ጠላት አጥፍቶ፣ አገር አስፍቶ እና በሃይማኖት ፀንቶ ሊኖር አይችልም። እነዚህ ባሉበት ከነገሠ ግን ሀገር ለመጠበቅና ሁሉን ነገር ለማድረግ ይቻለዋል። ይኸውም ከቀዳማዊ ምኒልክ ሲያያዝ መጥቶ እስከ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድረስ በእነዚህ 4 መናብርተ ጽዮን ግርማዊነታቸው ነግሠው 43 ዘመን ያለምንም እንከን ገዝተዋል። ግርማዊነታቸው ሲነግሡ የነበሩት የርእሰ አድባራት ወገዳማት አሰተዳደሪ ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰይፈ መንግሥትና ህለተ ወርቅ ያስጨበጡና ያስታጠቁ ፓትርያርክ አፈወርቅ ይባሉ ነበር። የመናብርተ ጽዮኑ ስያሜም 3ቱ በእመቤታችን ምሳሌ በጽዮን ስም አራተኛው የሊቀ ካህናቱ ታቦት ቅዱስ ሚካኤል ነው። ከእነዚህ ጋር ቀዳማዊ ምኒልክን ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ 12,000 መሣፍንትና መኳንንት ወይዛዝርት 1,500 በተግባረ ዕድ የሰለጠኑ የወርቅና የብር፣ የብረትና የመዳብ፣ እንዲሁም የነሐስ አንጥረኞች አዋቂዎች ጠቢባን ፀበርተ ዕፀውና ወቀርተ አዕባን ናቸው። እነዚህ ኢትዮጵያ ገብተው በየክፍለ ሀገሩ ሥራቸውን ሲጀምሩ አክሱም ጽዮን ትግራይ ላይ ስትቀር የዳዊት የወንድም ልጅ ሳቤቅ የሰሎሞን አጎት ከመጀመሪያው ፓትርያርክ አዛሪያስ ጋር ተከዜን ተሻግሮ አምሐራ ሳይንት ደረሰ። የአሁኗ ተድባበ ማርያም ካለችበት አምባ ላይ ሲደርስ ቤተ እግዚአብሔር መሥራት ጀመረ። ቦታዋንም በሀገሩ ስም ገሊላ ብሎ ጠራት። ፓትርያርክ አዛሪያስ ደስ አለውና ስሙን በቡራኬ አፀደቀለት። ለዚህችውም ተድባበ ጽዮን ቤተ መቅደሱን ሰርቶ ሲጨርስ ከሌዋውያኑም ከካህናቱም ከፍሎ መስዋተ ኦሪት የሚሰው ካህናትና ሌዋውያንንም ሾመ። መስፍኑ ሳቤቅ ቤተልሄማዊም በገፀ ንጉስ በወርቅ ወንበር የሚቀመጥ ነበር። ከዚህ ላይ ገሊላ ብሎ ከሰየመ በኋላ አገሮቹን አሻግሮ እያየ በሀገሩ ምሳሌ ይሰማቸው ጀመር። ደብረ ዘይት፣ ኬብሮን አሁን ከቀን ብዛት የተነሳ ህዝቡ ኬብሮንን ከሚኖር ይለዋል ይኽውም ከተድባበ ማርያም አምባ በር ወደ ምስራቅ ያለውን መግቢያ ነው። ወደ ቀኝ በኩል ተመልከተና እያሪኮ ትባል አለ ከቀን ብዛት ግን ሕዝቡ እያሪኮን አራሆ ይሏታል ቀጥሎ ኢየሩሳሌም ቀጥሎ ሎዛ ከዚህ ከሎዛ በላይ ታቦር አለው ይኸውም በአፄ በዕደ ማርያም ዘመን መግስት የተነሱት የቅኔ ፈጣሪዎች እነ ዮሐንስ ገብላአዊ፣ እነ ሠምራ አብ፣ እነ ወልደ ገብርኤል እነ ደቅ እስጢፋ የነበሩበት ነው።ከታቦር ቀጥሎ ሊባኖስ፣ ደማስቆ፣ አርሞንኤም፣ ደብር ፋራን፣ ደብረሲና አሁን ቦረና በመባል የሚጠራው ነው። በስተሰሜን በኩል ኮሬብ፣ ቃዴስ ደብረ ፍጌህ፣ ቂሣርያ፣ ቢታኒያ እና ጋዛ ፣ ጎልጎታ፣ ፌልስጥኤም ወዘተ ተብለው ተሰይመዋል። ይኸውም መታሰቢያነቱ ለ12 ነገደ እስራኤል እንደሆነ ይነገራል።
1. የበግ ምስልና እንደ ኮኮብ የሚያበራ የተቁለመለመ የበግ ቀንድ ያለበት መስቀል
2. ዐፄ ካሌብ ወደ ደቡብ አረቢያ የናግራንን (የመን) ክርስቲያኖች ለመርዳት ይዘውት የዘመቱት ጋሻ
3. የእብራይጥ ሲኖዶስና
4. የአረማይክ ቅዳሴ እግዚእ (ገበታ ቅዳሴ)
5. በአረማክ ቋንቋ የተጻፉ የስሌዳ መጻህፍት
6. 4. በአረበኛና በግእዝ የተጻፉ መጻህፍት
7. ወንጌል ዘወርቅ እየተባለ የሚጠራ ትልቅ የወርቅ ጉብጉብታ ያለበት ቅዱስ ወንጌል
8. የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጳጳስ የቀደሰበት የእጅ መስቀል
9. የመጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ መስቀል
10. የዕጨጌ ዮሐንስ በትረ ሆሳዕና እና የእጅ መስቀል
11. የአቡነ አኖሪዎስ የእጅ መስቀል
12. የአቡነ ቄርሎስ የእጅ መስቀል
13. ስእርተ ሀና (የማርያም እናት፣ ቅድስት ሀና ጸጉር)፣ የተቀመጠበት የሽክላ ገንቦ ጥንታዊና በስነ-ጥበባዊ ይዘቱ የሚያስገርም ነው
14. ሄሮድስ የጨፈጨፋቸው ህጻናት ዓጽም በክፊል
15. የቅዱስ ጊዩርጊስ አወራ ጣት
16. 13. በአጠቃላይ የ28 ሰማእታት ዓጽም ይገኛል
17. የዐፄ ገላውዴዎስን ጨምሮ የስድስት ነገስታትና የአራት እጨጌዎች ዓጽም ይገኛል
18. የአጼ ዳዊት ዙፋን
19. የቅዱስ የሬድ ድጓ እና ጊዩርጊስ ወልደ አሚድ፣ ገድለ አዳም
20. ከ1000 የሚበልጡ ጥንታዊ የብራና መጻህፍት
21. ሉቃስ እንዳሳላት የሚነገርላት የቅድስት ድንግል ማርያም ስዕለ አድህኖ
22. በርካታ ጥንታዊ የእጅና የመጾር መስቀል
23. 20.ልዩ ልዩ ንዋየ ቅድሳት
24. የነገስታት ዘውዶች፣ወንበርና አልባሳት
25. ባለ 3 ተከፍች የገበታ ስእልና ጥንታዊና ስነ ጥበባዊ ቅርሶች ይገኛሉ