ይህ የአማራ ትሥሥርር በቻይና ይፋዊ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ድረ-ገጽ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ልማድ፣ አርበኝነት፣ ቅርስ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችንም ጭምር ለአባላት በሚገባ እናሳውቃለን። የድረ-ገጹ ዋና አላማ የአማራን ታሪክ በሚገባ ለሁሉም በማስተማር ታሪካችንን ወደቀደመ ልዕልናው መመለስ ነው። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤ አንዲት ነጻ ሃገር ኢትዮጵያ -->

እቴጌ መነን አስፋው

 

እቴጌ መነን አስፋው እና ባለቤታቸው ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ

የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ባለቤት የነበሩት እቴጌ መነን አስፋው የተወለዱት መጋቢት 25 ቀን 1883 ዓ.ም ነበር። መነን የሚለው ቃል በአማርኛ ቋንቋ የሴት ልጅ ስም ሲሆን ታላቁ ምሁር ዓለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ቀጭን ፈታይ፣ ባለሟያ፣ መልከ መልካም፣ ትክክል፣ ፍጽምት፣ ሕጸጽ የሌለባት ማለት እንደሆነ ጽፈዋል። እቴጌ ማለትም የንጉሠ ነገሥቱ ሚስት፣ ባለዘውድ ማለት ሲሆን፤ የዐረቢኛው አታጂያ እቴጌ ጋር ተመሳሳይ ትርጓሜም አለው። በዐረብ ቋንቋ ታጅ ማለት ዘውድን የምትቀዳጅ ንግሥት ማለት ነው። የእቴጌይቱ የክርስትና ስም ወለተ ጊዮርጊስ ነው።

ግርማዊት እቴጌ መነን መጋቢት 25 ቀን 1883 ዓ.ም በወሎ ጠቅላይ ግዛት በአምባሰል አውራጃ ልዩ ስሙ ዕጓ በተባለ ቀበሌ ከአባታቸው ከዣንጥራር አስፋው እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ስኂን ሚካኤል ተወለዱ። በልጅነት ዘመናቸው በወላጆቻቸው ቤት መምህር ተቀጥሮላቸው አማርኛ ማንበብና መፃፍ ጠንቅቀው አወቁ፡፡ በተጓዳኝነትም ልዩ ልዩ የቤት ባልትና ሙያዎችን ተምረው በማጠናቀቃቸው የቤት ራስ ለመባል በቅተዋል። (ዣንጥራር  ለወሎ ባላባቶች በተለይም ለአምባሰል እና ዋድላ ደላንታ ሀገረ ገዢዎች ይሰጥ የነበረ ማዕረግ ነው)

በ1892 ዓ.ም ማለትም በተወለዱ በአሥረኛ ዓመታቸው ለመጀመሪያ ባለቤታቸው በሕግ ተዳሩ። ከእኝህ ባለቤታቸው ወይዘሮ በላይነሽ ዓሊንና ዣንጥራር አስፋው ዓሊን ወለዱ። ከዚያም ሁለተኛ ባለቤታቸውን በማግባት ዣንጥራር ገብረ እግዚአብሔር አመዴንና ወይዘሮ ደስታ አመዴን ወልደዋል። በ1903 ዓ.ም ራስ ልዑልሰገድ አጥናፍሰገድን አግብተው ነበር። ይህ ጋብቻ ሳይዘልቅ ቀረና በዚያው ዓመት የመጨረሻ ባለቤታቸውን ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ)ን አገቡ። ይህ ጋብቻ ፖለቲካዊ ተልዕኮ/ዓላማ ያለው ነበር። ይኸውም የእቴጌ መነን አጎት የሆኑትን የልጅ ኢያሱ ሚካኤልን እና የተፈሪ መኮንንን ሽኩቻና ፀብ ለማለዘብ ይጠቅማል ተብሎ በመኳንንቱ በተለይም በነራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው ተመክሮበት የተፈፀመ ነበር፡፡

ወይዘሮ መነን አስፋው ባለቤታቸው ልዑል አልጋ ወራሽ ንጉሥ ተፈሪ መኮንን ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ  ተብለው ሲነግሱ እርሳቸውም የእቴጌነት ዘውድ ጫኑ። ከጋብቻቸውም የሚከተሉትን ልጆች አፍርተዋል። ስማቸውም፦ 

                 1.  ልዕልት ተናኘወርቅን ኃይለሥላሴ፣ 

            2. ልዑል አስፋ ወሰን ኃይለሥላሴ፣

            3. ልዕልት ዘነበወርቅ ኃይለሥላሴ፣ 

      4. ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ፣ 

           5. ልዑል መኮንንን ኃይለሥላሴ እና 

            6. ልዑል ሳህለሥላሴን  ኃይለሥላሴን 

ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን እንደሚወር ይፋ በሆነበት ጊዜ እቴጌይቱ መስከረም 1 ቀን 1928 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ዕለት ለኢትዮጵያዊያን ብሎም ለዓለም ሴቶች ሁሉ የትግል ጥሪ አድርገዋል። ንግግራቸውም በዓለም ያላችሁ ሴቶች ሁሉ በዓለም ላይ እዉነተኛ ፍርድ እና ሰላም እንድነግሥ የመንግሥት ሰዎች ሁሉ በሚሰሩበት ሥራ በእግዚአብሔር መንፈስ እንዲመሩ በምናደርገው ጸሎት ተባባሪዎች እንዲትሆኑ የሚል ነበር። በኋላም እቴጌይቱ ግርማዊ ባለቤታቸው ጦር ሜዳ ሒደው ከጠላት ጋር ሲዋጉ እሳቸው በከተማው ያሉ ወይዛዝርቶችን እየሰበሰቡ ለቁስለኞች እና ለሰራዊቱ የሚሆን ስንቅ፣ ትጥቅ እና የህክምና ቁሳቁስ እያዘጋጁ ይልኩ ነበር። የከተማው ጸጥታ እንዲጠበቅ ከከተማው የዘበኛ ኃላፊዎች ጋር በመመካከር በትጋት እና በብርታት ሲሠሩ ቆይተዋል። በጦር ሜዳ ካሉት ከባለቤታቸው እና በዚያው ከሚገኙ የመረጃ ሰዎች የጣሊያን አውሮፕላኖች በአዲስ አበባ በሚኖረው ሰላማዊ ሕዝብ ላይ የቦንብ ጥቃት ለማድረስ እና ሕጻን፣ ሽማግሌ እና ሴት ሳይለይ በአንድነት ለመደምሰስ እየመጡ እንደሆነ በሥልክ በተላለፈ ጊዜ እቴጌ መነንንም በአውቶሞቢል ሆነው በድፍረት በከተማው እየዞሩ በመንገዱ እና በየገባያው ያለ ሕዝብ በአንድነት መቆሙን ትቶ እንዲበተን እና አደጋውን ወደሚከላከልበት ቦታ እንዲደበቅ በማደረግ ብሁ ሕዝብ ታድገዋል። ከዚህ በተጨማሪ በግል ንብረታቸው በኢትዮጵያና በኢየሩሳሌም በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንም አቋቁመዋል። ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳንጸዋል። ከነዚህም ለምሣሌ ለመጥቀስ ያክል የሐመረ ኖህ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያንን አሰርተው መጋቢት 16 ቀን 1910 ዓ.ም ታቦቷን በክብር አስገብተዋል።በ1925 ዓ.ም ደግሞ  የቅድስት ሐናን ቤተክርስቲያንን አሰርተዋል። በመስከረም ወር 1926 ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው በዮርዳኖስ ያሰሩትን የቅድሥት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እሣቸው በተገኙበት አስመርቀዋል።  በ1939 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ሰበታ ከተማ የምትገኘውን የጌቴሴማኒን ቤተክርስቲያን በገንዘባቸው አሠርተዋል። ለሴት ተማሪዎች ት/ቤት እንዲከፈት አድረገዋል። እቴጌ መነን አስፋው ባለቤታቸው ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እና አጎታቸው ልጅ ኢያሱ ሚካኤል በነበራቸው ፖለቲካዊ ፀብና አለመግባባት ምክንያት ሁለቱን ወገኖች ለማስማማት ብዙ ጥረት እንዳደረጉም ታሪካቸው ያስረዳል።

እቴጌ መነን አሰፋው የካቲት 9 ቀን 1954 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው፤ ሥርዓተ ቀብራቸውም በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል። በተቀበሩበት ዕለት ከተሰሙት እንጉርጉሮዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

የመኮነን እናት ምነው ምን  ነካዎ፣

ብዙ ጓደኞችዎን ጥለው መሔድዎ።

ኧረ ምን ይወራል ምን ትንፋሽ አለና፣

መነን ስታቋርጥ የሞትን ጎዳና።

መኮነን ገስግሶ ሥላሴ መግባቱ ፣

ቤት ሊሠራ ኑሯል ለወላጅ እናቱ።

በተቀበሩ በቀጣዩ ቀንም ባለኤታቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንግግር አድርገው ነበር። ንግግሩም፦ ኹላችሁም ከምታውቁት በላይ እኛ እራሳችን በቅርቡ የምናቃት ልንገልጠው የሚገባን ክፉ ቀን የማይለውጣት፣ ሃይማኖተኛ፣ በደጉም ጊዜ ዓላማችን ላይ ተጣልተን ሰው አስታርቆን የማያውቅ፣ ሣራ አብርሐምን እንደምትታዘዘው እሷም የእኛን ሃሳባችንን ፈጽማ የእግዚአብሔር ዳኝነት እስኪለየን ድረስ ለሕጻናትም ሆነ ለሽማግሌዎች ሕዝብም የሚጠቀምበት ጉዳይ ከምትረዳንም በላይ ራሷ ለማድረግ በምትጣጣረው ባሰራችሁ ሁሉ ተመስክሮ የተቀመጠ ነው ይል ነበር።

አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል


የአማራ ትስስር በቻይና

ጥቅምት 6  2015 ዓ.ም 

ቻይና

የአማራ ትስስር በቻይና(ANiC)

የአማራ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ፣ ሃይማኖትና ባህል ያለው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት የሆነ፤ ሃገር የሰራ፣ ነጻነቱን ያስጠበቀ፤ የራሱ የሆነ ፊደል ያለው፤ የጥንታዊ ትምህርት ስርዓት ባለቤት የሆነ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ በሃገረ መንግስት ምስረታ ሃገርን ከወራሪ መጠበቅና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ታላቅ ገድል በመስራት እኛ ልጆቹ ቀና ብለን እንድንሄድ አድርጎናል።

Post a Comment

ቀዳሚ ገጽ ተከታይ ገጽ
hi