ይህ የአማራ ትሥሥርር በቻይና ይፋዊ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ድረ-ገጽ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ልማድ፣ አርበኝነት፣ ቅርስ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችንም ጭምር ለአባላት በሚገባ እናሳውቃለን። የድረ-ገጹ ዋና አላማ የአማራን ታሪክ በሚገባ ለሁሉም በማስተማር ታሪካችንን ወደቀደመ ልዕልናው መመለስ ነው። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤ አንዲት ነጻ ሃገር ኢትዮጵያ -->

የንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ የእረፍት እና የንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ የንግሥና መታሰቢያ ዕለት

 ጥቅምት 12  የንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ የእረፍት እና የንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ የንግሥና መታሰቢያ ቀን  ነው። ዛሬ ማለትም ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም የንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ የ175ኛ ዓመት መታሰቢያ ቀን ነው።  ስም ጥሩና ገናናው የሸዋ ንጉሥ፣ ንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ ያረፉት ከዛሬ 175 ዓመታት በፊት ጥቅምት 12 ቀን 1840 ዓ.ም ነበር። ልጃቸው ንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ (የዳግማዊ አፄ ምኒልክ አባት) የሟች አባታቸው ዙፋን የተኩትም ከዛሬ 175 ዓመታት በፊት ጥቅምት 12 ቀን 1840 ዓ.ም ነበር።

ንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ የራስ ወሰንሰገድ አስፋወሰን እና የወይዘሮ ዘነበወርቅ ጎሌ ልጅ ናቸው።  የተወለዱት በ1788 ዓ.ም ነው።  በዘመኑም ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የሚገዛ ምኒልክ የሚባል ንጉሥ ይነግሣል የሚባል ንግርት ስለነበር፣ አባታቸው ራስ ወሰንሰገድ ምኒልክ የሚል ስም አውጥተውላቸው ነበር። አባታቸው ራስ ወሰንሰገድ አስፋወሰን ሲሞቱ ሰኔ 1 ቀን 1806 ዓ.ም በ18 ዓመታቸው የአባታቸውን አልጋ ወርሰው ሸዋን ማስተዳደር ጀመሩ።


ንጉሥ ሳህለሥላሴ ከሸዋ ባላባቶች መካከል (ከነጋሲ ክርስቶስ እስከ ኃይለመለኮት ድረስ ካሉት ገዢዎች መካከል) ኃያሉ፣ ሰፊ ግዛትና ብዙ ሀብት የነበራቸው እንደሆኑ ታሪካቸው ያሳያል፡፡ በወቅቱ በዓለም ላይ ኃያላን ከነበሩት ከብሪታኒያና ከፈረንሳይ መንግሥታትም ጋር የንግድና የወዳጅነት ስምምነት መፈራረማቸውም የዚሁ ኃያልነታቸው ማሳያ ነው። ንጉሥ ሣህለሥላሴ ሸዋ ገዢ በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት አገዛዝ ላይ ትገኝ ስለነበር አንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ባለመኖሩ እርሳቸው ኃይላቸውን በማጠናከር አንኮበርን መሰረት አድርገው ግሼ፣ ግድም፣ ኤፍራታ፣ አንጾኪያ፣ ይፋት፣ መርሐቤቴ፣ ላምዋሻ፣ ሞረት፣ እንሳሮ፣ አህያፈጅ፣ ቀይ አፈር፣ ቡልጋ፣ ምንጃር የተባሉትና አፋር ድረስ ያሉ ብዙ ቦታዎች በአስተዳደራቸው ስር እንዲሆኑ አድርገው ነበር። ንጉሥ ሳህለሥላሴ በአስተዳደር ዘመናቸው የተቸገረን የሚረዱ፤ አቅም ላጣ ግብሩን የሚምሩ፤ ዕዳ ላለበት ዕዳውን የሚከፍሉ እንዲሁም ጥማድ በሬ ለሌለው ጥማድ እየሰጡ እረስ ቆፍር እያሉ ሕዝባቸውን ለሥራ የሚያበረቱ ነበሩ። እነዚህን በመሳሰሉ መልካም ሥራቻቸው የተነሳም በሕዝቡ ዘንድ በጣም ይወደዱ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል። 

የአሁኗ አዲስ አበባም ገና ከመመስረቷ በፊት ንጉሥ ሣህለሥላሴ መንግሥታቸውን (ግዛታቸውን) ለማስፋት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ አሁን የምኒልክ ቤተመንግሥት ወደሚገኝበት አካባቢ መጥተው ድንኳን ተክለው በመቀመጥ አንቺ ቦታ የልጅ ልጄ ትልቅ ከተማ ይቆረቁርብሻል … የልጅ ልጄ እዚች ቦታ ላይ ከተማ ይሰራባታል ብለው ትንቢት ተናግረው ነበር ይባላል። ይህ ትንቢታቸውም የልጅ ልጃቸው በሆነት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ፍጻሜ አገኘ (እውን ሆነ)። 

በመጨረሻም ንጉሥ ሣህለሥላሴ ለ33 ዓመታት ከ 5 ወራት ያህል ሸዋንና በሸዋ ዙሪያ ያለውን ቦታ ሲያስተዳድሩ ቆይተው ከዛሬ 175 ዓመታት በፊት (ጥቅምት 12 ቀን 1840 ዓ.ም) ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ስርዓተ ቀብራቸውም ራሳቸው ባሰሩት በአንኮበር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል። 

የንጉሥ ሳህለሥላሴን ሞት ተከትሎ ዙፋኑን የወረሱት ልጃቸው ንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ ነበሩ። የንጉሥ ኃይለመለኮት እናት ወ/ሮ በለጥሻቸው ወልዴ ይባላሉ። ንጉሥ ኃይለመለኮት በሰውነታቸው ግዝፈትና ጥንካሬ እንዲሁም በልባቸው ቀናነት በሸዋ ዘንድ የታወቁና የተወደዱ ንጉሥ ነበሩ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የኢትዮጵያ ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚነግሩን ንጉሥ ኃይለመለኮት ከጥንካሬያቸው የተነሳ ኢላማ ተኩስ በሚተኩሱ ጊዜ መሳሪያውን አጠንክረው በመያዛቸው ምክንያት ጥይቱ ሲወጣ ጠመንጃቸው ለሁለት ተሰብሮ እጃቸው ላይ ቀርቶ ያውቃል።

ንጉሥ ኃይለመለኮት ሸዋን ለ8 ዓመታት አስተዳድረዋል። በስልጣን ላይ ሳሉም ተቀናቃኝ ሊሆኑባቸው የሚችሉትን ወገኖቻቸውን እንዲያስሯቸውና እንዲያስወግዷቸው ሰዎች ሲመክሯቸው ተዉ! ይሄን አላደርገውም! እግዚአብሔር የወደደውን ነው የሚያስገዛው የሚሉ ቀና ሰው እንደነበሩ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በመጽሐፋቸው ጠቅሰውታል።

በመጨረሻም ዳግማዊ ዐጼ ቴዎድሮስ በሀገሪቱ በየቦታው ያለውን የተከፋፈለ አገዛዝ ወደ አንድ አስተዳደር በማምጣት በማእከላዊ መንግሥት ስር የምትተዳር አንዲት ሀገር ለመመስረት አስበው ከየመሳፍንቱ ጋር በሚዋጉበት ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ሸዋም ሊመጡ ነው የሚል ወሬ ተሰምቶ ንገሥ ኃይለመለኮትም ለጦርነት ተዘጋጁ፤ ሆኖም ግን ከጦርነቱ ቀደም ብሎ ንጉሥ ኃይለመለኮት ታመው ነበርና እርሳቸው በጦርነቱ ሳይካፈሉ ጥቅምት 30 ቀን 1848 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። 

ምንጭ፦ (ልዑል አምደ ፅዮን)፤ (የደብረብረሃን ቱሪዝም ልማት ፕሮግራም)

አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል


የአማራ ትስስር በቻይና

ጥቅምት 12  2015 ዓ.ም 

ቻይና

የአማራ ትስስር በቻይና(ANiC)

የአማራ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ፣ ሃይማኖትና ባህል ያለው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት የሆነ፤ ሃገር የሰራ፣ ነጻነቱን ያስጠበቀ፤ የራሱ የሆነ ፊደል ያለው፤ የጥንታዊ ትምህርት ስርዓት ባለቤት የሆነ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ በሃገረ መንግስት ምስረታ ሃገርን ከወራሪ መጠበቅና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ታላቅ ገድል በመስራት እኛ ልጆቹ ቀና ብለን እንድንሄድ አድርጎናል።

2 Comments

ቀዳሚ ገጽ ተከታይ ገጽ
hi