የልሂቃን የጥበበኞች እና የጀግኖች ሀገር ሸዋ
የፊደል ገበታው ጌታ ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሄረ-ቡልጋ
ቀኝ አዝማች ተስፋ ከአባታቸው ከመምህር ገብረሥላሴ ቢልልኝ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሥዕለሚካኤል ወልደአብ ታህሳስ 24፣1895 ዓ.ም ተወለዱ። የፊደል ገበታ አባት የሚል ቅፅል መጠሪያ ያገኙት ተስፋ ገብረሥላሴን የሕይወትና የሥራ ታሪክ የሚያስቃኘው መፅሐፍ፤ ስለአማርኛ የፊደል ገበታ ፈጣሪዎች ማንነትና ዘመን ማብራሪያ ባይኖረውም፣ ባለታሪኩ በመጀመሪያ በብራና ላይ በእጃቸው እየፃፉ፣ በመቀጠልም በማተሚያ ቤት ማሽን እያባዙ ለህዝብ እንዲደርስ አድርገዋል።
የአማርኛ የፊደል ቅርፅ በወቅቱ በእንጦጦ ማርያም፣ በባዕታ ለማርያምና በመካነ ኢየሱስ ሥላሴ አጥቢያዎች እንዲሁም በገጠር አብያተ ክርስትያናት፤ በገዳማትና በዋሻዎች ብቻ ተወስኖ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ፍንጭ አጥኚዎች የፊደል ገበታውን በእነዚህ ተቋማት ያኖረው ሰው ማነው ብለው እንዲጠይቁ የሚያግዝ ጥቆማ ነው። ተስፋ ገብረሥላሴ በ1909 ዓ.ም የ15 ዓመት ልጅ ሆነው ከትውልድ መንደራቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ያረፉበት መንደር አራት ኪሎ ነበር። በዚያ ዘመን ከአራት ኪሎ የከተማዋ ደማቅ አካባቢ፤ አዝማሪ የማይታጣበት የቆንጆዎች መቀጣጠሪያ ነበር ይላል በመፅሃፉ ገፅ 29 የሰፈረው መረጃ። ተስፋ ገብረስላሴ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ሰርተው ራሳቸውን ለመቻል በእንጨት ፈለጣ፣ ውሃ በመቅዳት፣ ጉድጓድ በመቆፈር፣ በጎዳና ንግድ እና መሰል ትናንሽ ስራዎች ላይ ተሳትፈዋል። ነጋድራስ አቡበከር ከጅቡቲ ከሚያስመጧቸው በተለይ ሽቶ እየተቀበሉ በየሆቴሉ ዞረው ሸጠዋል። በዘመኑ በአራት ኪሎ መንደር በንግድ ስራቸው በጣም ታዋቂ የነበሩት ነጋድራስ አቡበከር የአፋር ብሄረሰብ ተወላጅ ነበሩ። ከፈረንሳይ አገር የሚያስመጡትን ሸቀጥ በጅቡቲ በኩል ወደ አዲስ አበባ በማስገባት አገልግሎት ሲሰጡ በዕድሉ ከተጠቀሙት አንዱ ነበሩ።
ክስ፣ እስርና ውንጀላ ያልተለያቸው ባለታሪክ የተስፋ ገብረሥላሴን የስራና የህይወት ታሪክን ማዕከል አድርጎ የአገራችንን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጉዳዮች በስፋት የሚያስስ ዘመን ተሻጋሪ ባለ-ውለታ መፅሐፍ፤ ባለ ታሪኩ የህዝብና የአገር ባለውለታ መሆን የቻሉት በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው እንደሆነ ይገልፃል። በንጉሡ ዘመን (ከኢጣሊያ ወረራ በፊትና በኋላ) ፣በጠላት ወረራ ወቅት፣ በደርግም አገዛዝ ለክስ፣ ለእስርና ውንጀላ ተዳርገዋል፡፡ በመጨረሻ ሁሉንም አሸንፈው በተደጋጋሚ ተሸላሚ ሆነዋል።
ከአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት የቀኝ አዝማች ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ደጋግሞ አመስግኗቸዋል። ታላቅ ተግባርና ትልቅ ስም አርቆ መድረሻን ለማቀድ፣ ከብዙ ጥረትና ልፋት የሚገኝ ነው። በዓመታት ድካም የተገነባ መልካም ተግባርና ስም ሊጠፋ፣ ሊረሳና ሊዘነጋ የሚችልባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። እኔ ከሞትኩ በኋላ ጥረትና ድካሜ ምን ይሆናል ብሎ ቀድሞ አለማሰብ ታላቅ ተግባርና ስም እንዲጠፋ ሰበብ ከሚሆኑት አንዱ ነው።ቤተሰቦቻቸውን ባለ አክሲዮን በማድረግ ኃ.የተ.የግ.አ/ማህበር በ1991ዓ.ም ያቋቋሙት ባለታሪኩ፤ ሥራና መልካም ተግባራቸው እንዳይጠፋ ማድረግ ችለዋል።
ተስፋ ገብረሥላሴ ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ የ97 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ነበሩ።
ምንጭ፦ ከመታገስ ዋሌ ( ቆራጡ አማራ ገጥ ላይ የተወሰደ )

