ይህ የአማራ ትሥሥርር በቻይና ይፋዊ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ድረ-ገጽ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ልማድ፣ አርበኝነት፣ ቅርስ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችንም ጭምር ለአባላት በሚገባ እናሳውቃለን። የድረ-ገጹ ዋና አላማ የአማራን ታሪክ በሚገባ ለሁሉም በማስተማር ታሪካችንን ወደቀደመ ልዕልናው መመለስ ነው። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤ አንዲት ነጻ ሃገር ኢትዮጵያ -->

በየነ ወንድማገኘሁ

ደጅአዝማች በየነ ወንድማገኘሁ(አባ ሰብስብ)

ከደጅ አጋፋሪነት እስከ ሊጋባነት፣ ከደጅ አዝማችነት እስከ ሀገረ ገዥነት የደረሱ፤ ከምኒልክ እስከ እያሱ፤ ከዘውዲቱ እስከ ኃይለሥላሴ ሀገራቸውን ያገለገሉ የ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ የኢትዮጵያ ባለውለታ እና ሀገር ወዳድ ናቸው። ሀገር እና ንጉሥ ለየቅል ናቸው ብለው የሚያምኑ፤ ንጉሥ ቢበድላቸው ሀገር የማያኮርፉ በሳል፣ አርቆ አሳቢ፣ እምቢ ባይ እና ጀግና ናቸው። በፈረስ ስማቸው አባ ሰብስብ ይሏቸዋል፤ እምቢተኝነታቸውን መሰረት ያደረገው እና እስከዚህ ትውልድ የደረሰው መጠሪያቸው ግን ሊጋባው በየነ ነው፤ ደጅአዝማች በየነ ወንድማገኘሁ።

በ 1868 ዓ.ም. እንደተወለዱ የሚነገርላቸው በየነ አባ ሰብስብ የትውልድ አካባቢያቸው ሸዋ ቡልጋ ውስጥ ነው። ቡልጋ አካባቢ በሚገኝ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው እንደተማሩ የሚነገርላቸው አባ ሰብስብ ወደ አንኮበር አቅንተውም የቅኔ፣ የመጽሐፍትና የቤተ መንግሥት ትምህርት ቀስመዋል። ወደ ሥራው ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰማሩም በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት በደጅ አጋፋሪነት ተመድበው ነበር። በልጅ እያሱ ዘመነ መንግሥት ከአጋፋሪነት ወደ ሊጋባነት ከፍ ያሉበትን ሹመትም አግኝተዋል። በ1909 ዓ.ም ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ነግሠው ተፈሪ መኮንን ደግሞ ባለሙሉ ሥልጣን አልጋወራሽ ሲሆኑ ሊጋባው በየነ በደጃዝማችነት ማዕረግ መጀመሪያ በባሌ ከወራት በኋላ ደግሞ ወደ ወላይታ ተዛውረው አውራጃ ገዢ ሆነው ተሹመው አገልግለዋል።

ለአምስት ዓመታት ያክል ወላይታን እንዳስተዳደሩ በ1915 ዓ.ም ሀገረ ገዢው ደጃዝማች በየነ ወንድምአገኘሁ ላይ ክስ ተመሰረተ። ክሱን ለመመርመር ግራዝማች ቆርቾ የሚባሉ የአልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን ሹም ከአዲስ አበባ ወደ ወላይታ ተላኩ። ጉዳዩ ከተመረመረ በኋላ ክርክሩ አዲስ አበባ ቢደረግ የሚሻል መስሎ ስለታያቸው ለበላይ አካል አስታወቁ። ክሱ አዲስ አበባ ከልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ችሎት ቀርቦ ከተመረመረ በኋላ ግንቦት 9 ቀን 1915 ዓ.ም በደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁ ላይ ስለተፈረደባቸው በመጀመሪያ በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ቤት ዘጠኝ ወር ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አንኮበር ከተማ ተዛውረው ዘጠኝ ወር ታሰሩ። ከአንኮበር እስረኝነት አመክሮ ተደርጎላቸው በወርሃ ጥር እስራቱ በምሕረት ተቀየረላቸውና ወደ አዲስ አበባ ሳይገቡ በርስታቸው ላይ እንዲቀመጡ ተወሰነ።

አባ ሰብስብ ለድጋሚ እስር የሚዳረጉበት ሌላ ክስተት ተፈጠረ። በርስታቸው ላይ ሳሉ ለጦር ሚኒስትሩ ለፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲኔግዴ በሚስጥር ደብዳቤ እየላኩ በአልጋወራሹ ላይ ሴራ ለማሴር ሞክረዋል ተባለ። ደብዳቤዎን ለልዑል አልጋወራሽ ያቀረቡትም ራሳቸው የጦር ሚኒስትሩ ናቸው እየተባለ ይነገራል። ደጃዝማች በየነ ከልዑል አልጋወራሽ ችሎት ቀረቡ። ለአባ መላ ሀብተ ጊዮርጊስ የተጻፈው ደብዳቤ የሳቸው መሆን አለመሆኑን የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠየቁ። እርሳቸውም የራሳቸው ቃል እንደሆነ በድፍረት ከኃይለ ቃል ጋር ተናገሩ። ፈራጆች ተራ በተራ እየተነሡና እየተቹ ያስቀጣል እያሉም ፈረዱባቸው።

አልጋወራሹን ኃይለ ቃል እንደተናገሩ የሚነገርላቸው አባ ሰብስብ በጅራፍ እንዲገረፉም ተደርጓል አሉ። እስር ተፈርዶባቸውም በዕለቱ ወደ ሀረር እንዲሄዱ ተደረገ። ሊጋባው በየነ በሀረር እስር ላይ እያሉ አልጋወራሽ ተፈሪ 1921 ዓ.ም ንጉሥ ተፈሪ ተብለው ሲነግሡ የንግሥና በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ በምህረት ተለቀቁ። ከእስር እንደተለቀቁም ንጉሥ ተፈሪ መኮንን የጎንደር ሀገረ ገዢ አድርገው ሾሟቸው። ነገር ግን አባ ሰብስብ ሀገሬን እንጂ ያሰረኝን እና የገረፈኝን ሥርዓት ዳግም አላገለግልም በማለት ሹመቱን ሳይቀበሉት ቀሩ። ሹመቱን አልቀበልም ሲሉም በንጉሡ ላይ ሌላ ኃይለ ቃል ተናግረዋል ተብሎ ወደ ኮንታ በግዞት ተላኩ። አባ ሰብስብ ሹመት እምቢ ብሎ መታሰሩን የሰማው የሀገሬው ሰውም እንዲህ ሲል ተቀኘላቸው።

ጠጅ ጠጣ ሲሉት ውኃ እየለመነ፤
እንደ ኮራ ሄደ እንደ ተጀነነ፤
የጎንደር ባላባት ሊጋባው በየነ።

ጠጁ የጎንደር የሀገረ ገዥነት ሹመት ሲሆን ውኃው ደግሞ የኮንታ ቅዝቃዜ መሆኑ ነበር። ይህ ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ አባ ሰብስብ በእስር ላይ እንዳሉ ፋሺስት ጣሊያን ዳግም ሀገሪቱን መውረሩ ተሰማ። ሀገሬን እንጂ ያሰረኝን እና የገረፈኝን ሥርዓት አላገለገልም ያሉት ደጅአዝማች በየነ ወንድማገኝ ፋሺስት ሀገሪቱን መውረሩን ሲሰሙ ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ደብዳቤ ጻፉ።

የጎን ሕመም ቁስሉን በይቅርታ አልብሶ፣
ስለክብርሽ ሲባል ገባልሽ ገስግሶ።

እንደተባለላቸው ለደጃዝማች በየነ ወንድማአገኘሁ እስራት፣ ግርፋት፣ ሕመምና ቅያሜ ሌላ ጉዳይ ነው። ይህን ሁሉ ማሰላሰል፣ ማውጣትና ማውረድ የሚቻለው እናት ሀገር ስትኖር ነው። እናም የመጣብንን የጋራ ጠላት ለመፋለም በእኔ በኩል ቁርጥ አድርጊያለሁ ብለው ሀገራቸውን ከወራሪ ነጻ ለማድረግ ያላቸውን አቋም በማሳወቅ ንጉሠ ነገሥቱ ጥያቄያቸውን ተቀብለው በጦርነት እንዲያሰልፏቸው ተማጽነዋል። ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ከኮንታ እስር ቤት ወጥተው ወደ ጦር ግንባርም ዘመቱ።

መስከረም 1928 ዓ.ም. የታወጀውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የክተት አዋጅ ተከትሎ በሰሜን ኢትዮጵያ የመጣውን የፋሽስት ወራሪ ጦር ለመመከት በቤጌምድር እና በሰላሌ ገዥ በልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ዋና ጠቅላይ አዝማችነት ይመራ በነበረው የሰሜን ጦር ውስጥ አባ ሰብስብ ተቀላቀሉ። በተንቤን ግንባር ውጊያ ላይ የነበሩት አባ ሰብስብ የካቲት 19 /1929 ዓ.ም ተንቤን ላይ በነበረው ጦርነት በጀግንነት ሲዋጉ እና ሲያዋጉ ውለው አመሻሽ ላይ በጀንግነት ተሰው። በማይጨው ግንባር ዘምተው እያለ የደጃዝማች በየነን መሰዋት የሰሙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም አንተ ግንባርክን ለሀገርህ እንደሰጠህ እኛ ደግሞ ያለምንም ስስት ደረታችንን ለሀገራችን እንሠጣለን ሲሉ የአባ ሰብስብን ጀግንነት መሰከሩ። እድሜ ዘመናቸውን አሳሪ እና ታሳሪ ሆነው የዘለቁት ተፈሪ መኮንን እና ሊጋባው በየነ ሀገር አንድ አድርጋ ለየቻቸው። ኢትዮጵያ ስለእርሷ ሲሉ መበደላቸውን የሚረሱ ልጆች ባለቤት ነች ሀገረ ገዥነትን ለናቁባት ኢትዮጵያ ከመሞት በላይስ የሚከፈል ምን ዋጋ ይኖራል። ኢትዮጵያ በልጆቿ መራር ተጋድሎ ታሸንፋለች።
ምስል፦ ሊጋባው በየነ


የአማራ ትስስር በቻይና

ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም

ቻይና

የአማራ ትስስር በቻይና(ANiC)

የአማራ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ፣ ሃይማኖትና ባህል ያለው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት የሆነ፤ ሃገር የሰራ፣ ነጻነቱን ያስጠበቀ፤ የራሱ የሆነ ፊደል ያለው፤ የጥንታዊ ትምህርት ስርዓት ባለቤት የሆነ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ በሃገረ መንግስት ምስረታ ሃገርን ከወራሪ መጠበቅና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ታላቅ ገድል በመስራት እኛ ልጆቹ ቀና ብለን እንድንሄድ አድርጎናል።

Post a Comment

ቀዳሚ ገጽ ተከታይ ገጽ
hi