ይህ የአማራ ትሥሥርር በቻይና ይፋዊ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ድረ-ገጽ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ልማድ፣ አርበኝነት፣ ቅርስ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችንም ጭምር ለአባላት በሚገባ እናሳውቃለን። የድረ-ገጹ ዋና አላማ የአማራን ታሪክ በሚገባ ለሁሉም በማስተማር ታሪካችንን ወደቀደመ ልዕልናው መመለስ ነው። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤ አንዲት ነጻ ሃገር ኢትዮጵያ -->

የኢትዮጵያ ወራት አሰያየም እና አመጣጥ

የኢትዮጵያ ወራት አሰያየም እና አመጣጥ

በኢትዮጵያ የወራት ስሞች ከጥንት ጀምሮ የነበሩ፤ እርስ በርስ የተወራረሱ ናቸው። የአማርኛ የወራት አሰያየም ከተወሰነ የድምጽ ልዩነት በስተቀር ከግእዙ ጋር አንድ ነው። ይህ መመሳሰል ደግሞ አማርኛው ከግእዙ በውሰት ወስዶት እንደሆነ መገመት ይቻላል። ምክንያቱም ቋንቋው የመጣው ከግእዝ በኋላም ሰለሆነ ነው። አእምሮ ጌታሁን(2000፡103 - 104) ከጥቅምት በስተቀር ከመስከረም እስከ ነሐሴ ያሉት የአማርኛ የወራት ስሞች ከግእዝ ግሶች እንደመጡ ያስረዳል። በዚህም መሰረት፦

መስከረም ‘ዘከረ’፣ ጥቅምት ‘ጠቀመ’፣ ህዳር‘ኀደረ’ (አማርኛው አደረ ማለት ነው)፣ ታኅሳስ ‘ኀሠሠ’( አማርኛው ፈለገ ማለት ነው)፣ ጥር ‘ጠረየ’(አማርኛው ሰበሰበ ማለት ነው)፣ የካቲት ‘ከተ’(አማርኛው ከተተ ማለት ነው)፣ መጋቢት ‘መገበ’( አማርኛ መገበ፣ ቀለበ ማለት ነው)፣ ሚያዚያ ‘ምዕዘ’(አማርኛ ሸተተ ማለት ነው)፣ ግንቦት ‘ገነበ’(አማርኛው ገነባ ማለት ነው)፣ ሰኔ ‘ሠነየ’(አማርኛው አማረ ማለት ነው)፣ ሐምሌ ‘ሐመለ’ (አማርኛው ለመለመ ማለት ነው) ነሐሴ ‘ነሐሰ’(አማርኛ ሠራ፣ ገነባ ማለት ነው) (ምንጭ ፦ አዕምሮ ጌታሁን 2000፡ 103 -104)

ከመስከረም እስከ ጳጉሜ ያሉት ወራት እንዴት ተሰየሙ?


፩. መስከረም የግእዝ ስርወ ቃሉ - መስ እና ከረም ትርጉሙም መስ ማለት አለፈ ሲሆን ከረም ማለት ደግሞ ክረምት ማለት ነው። መስከረም ማለት ክረምት አለፈ ማለት ነው። የመስከረም ወር አበቦች በየመስኩ የሚፈነዱበት፤ አደይ አበባ ምድሪቱን የሚያለብስበት ወር ነው።

፪. ጥቅምት የግእዝ ስርወ ቃሉ ጠቀመ ትርጉም ሠራ፣ጠቃሚ ጊዜ ማለት ነው። በገበሬው ዘንድ የጥቅምት ወር የሚታወቀው ጥራጥሬ ተዘርቶ እሸት የሚያፈራበት ወር በመሆኑ ነው። ይህ ወር ከሌላው ወር በበለጠ ለገበሬው እና ለከብቶቹ ጠቃሚ ወር ነው። በመሆኑም ጥቅም የሚሰጥ ጠቃሚት ወይም ጥቅምት ተብሎ የተጠራው በዚህ ምክንያት ነው።

፫. ኅዳር የግእዝ ስርወ ቃሉ ኀደረ ትርጉም አደረ፣ ሰው በወርሃ አዝመራ ማሳ ውስጥ ለጥበቃ ማደሩን ይገልፃል።

፬. ታኅሳስ የግእዝ ስርወ ቃሉ ኀሠሠ ትርጉም መረመረ፣ ፈለገ ማለት ነው። በመኽር ወቅት የሰብል ምርመራ ያመለክታል።

፭. ጥር የግእዝ ስርወ ቃሉ ነጠረ ነው። ትርጉም ጠረረ፣ ብልጭ አለ፣ ነጻ፣ በራ የፀሐይን ግለት ወቅት ያሳያል።

፮. የካቲት የግእዝ ስርወ ቃሉ ከቲት ትርጉም (የእህልን) መክተቻ ማለት ነው። በገበሬው ዘንድ እህል ተሰብስቦ ወደ ጎተራ የሚከተትበት ወር ነው። በመሆኑም የመክተቻ ወር መሆኑን ለማመልከት የካቲት ተባለ። ከቲት ማለት ከታች ማለት ሲሆን፤ የካቲት ደግሞ የመክተቻ ጊዜ እንደማለት ነው።

፯. መጋቢት የግእዝ ስርወ ቃሉ መገበ ትርጉም በቁሙ የሚመግብ (በጎተራ የተከተተው የሚበላበት) ማለት ነው። የመጋቢት ወር ፍቺ ግልጽ ነው። ምግብ የሚመግበውን መጋቢ፤ አንስታይ ጾታ ወይም ሴት ከሆነች ደሞ መጋቢት ይለዋል። ጥቅምት ጠቃሚ ወር በመሆኑ፤ ጠቃሚቷ ወር ጥቅምት ተብላለች። አሁን ደግሞ ምግብ ሰጪ እና መጋቢ የሆነውን ወር መጋቢት ያሉት ያለ ምክንያት አይደለም። በዚህ የበልግ ወር እህል እና ጥራጥሬ ብቻ ሳይሆን፤ ወፍ ዘራሽ እና የጫካ ፍራፍሬዎች ጭምር በየስፍራው ያድጋሉ። እንሰሳት እና አእዋፋትም እንደልባቸውና እንደሆዳቸው መጠን የሚመገቡበት ወር ስለሆነ፤ ይህን የምግብ እና የጥጋብ ወር መጋቢ ወይም መጋቢት ብለው ጠሩት።

፰. ሚያዚያ የግእዝ ስርወ ቃሉ መሐዘ ትርጉም ጎረመሰ ጎበዘ ሚስት ፈለገ(ወርኀ ሰርግ መሆኑን ሲያጠይቅ)። በአረብኛ ማዛ ማለት መልካም ወይም ጥሩ መዓዛ ያለው ሽታ ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ሚያዝያን ከመልካም ሽታ ጋር ያያይዙታል። እውነታው ግን ወዲህ ነው። ከላይ እንዳየነው ሚያዝያ የሚለው ቃል የሚወለደው፤ “መሐዘ” ከሚለው የግዕዝ ቃል ነው። እንደልማድ ሆኖ ከግንቦት ወር ጀምሮ ሰርግ አይደረግም። ስለዚህ የጎለመሰ ወይም የመሐዘ ሰው፤ ሚዜ አደራጅቶ ሚስት የሚያገባው ከግንቦት ወር ቀድሞ በሚገኘው ወር ነው። በዚህ ምክንያት ወሩም ትዳር መያዣ ወይም መሐዘ መሐዘያ መያዥያ ተብሏል።

፱. ግንቦት የግእዝ ስርወ ቃሉ ገነበ ትርጉም ገነባ፣ ሰራ፣ ቆፈረ፣ ሰረሰረ(ለእርሻ የመሬቱን መዘጋጀት ያሳያል። በዚህ ወር መሰረት ተቆፍሮ ግንባታ የሚጀመርበት ነው። ለምሳሌ ፈለገ የሚለው ቃል ፍላጎት እንደሚባለው፤ ሰረቀ ብሎ ስርቆት እንደሚባለው፤ ገነባ ብሎ ግንቦት ይላል። በአገራችንም በዚህ ወር በርካታ የግንባታ ስራዎች ይከናወናሉ። የአባይ ግድብ ጭምር የተጀመረው በግንቦት ወር ነው።

፲. ሰኔ የግእዝ ስርወ ቃሉ ሠነየ ትርጉም አማረ፣ ሰናይ ሆነ፣ መልካም ሆነ ማለት ነው።

፲፩. ሐምሌ የግእዝ ስርወ ቃሉ ሐመለ ትርጉም ለመለመ ማለት ነው። በሐምሌ ወር ክረምት ይገባና ልምላሜ ይጀምራል። የለመለመ ነገር ደግሞ ሐመልማል ይባላል።

፲፪. ነሐሴ የግእዝ ስርወ ቃሉ አናህስየ ትርጉም አቀለለ፣ ተወ የክረምቱን እያደረ መቅለሉን ያመለክታል።

፲፫. ጳጉሜ ስርወ ቃሉ ግሪክ ሲሆን ኤጳጉሚናስ በእንግሊዘኛው ደግሞ epagomenal ኤፓጎሜናል ይባላል ትርጉመም፤ ተጨማሪ ወርህ እንደማለት ነው።

አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል ከቴክኖሎጂ ክፍል ጋር በመተባበር

የአማራ ትስስር በቻይና

ነሐሴ 01 ቀን 2014 ዓ.ም

ቻይና

የአማራ ትስስር በቻይና(ANiC)

የአማራ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ፣ ሃይማኖትና ባህል ያለው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት የሆነ፤ ሃገር የሰራ፣ ነጻነቱን ያስጠበቀ፤ የራሱ የሆነ ፊደል ያለው፤ የጥንታዊ ትምህርት ስርዓት ባለቤት የሆነ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ በሃገረ መንግስት ምስረታ ሃገርን ከወራሪ መጠበቅና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ታላቅ ገድል በመስራት እኛ ልጆቹ ቀና ብለን እንድንሄድ አድርጎናል።

Post a Comment

ቀዳሚ ገጽ ተከታይ ገጽ
hi