💫የአሸንድዬ በዓል በላስታ ቅዱስ ላሊበላ💫
የአሸንድዬ በዓል በነሐሴ ወር አጋማሽ የጾመ ፍልሰታ ለማርያምን ፍጻሜ ተከትሎና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በዐለ ዕርገት መሠረት አድርጎ የሚከበር ነው። ፍልሰታ የሚለው ቃል የድንግል ማርያምን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፤ ኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ቃል ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱ በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፻፴፩ ፥፰ ላይ ተነሥዕ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ (አቤቱ ወደ ዕረፍትኽ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስኽ ታቦት) የሚለው ነው። ጾመ ፍልሰታ በፍትሐ ነገሥት በአንቀጽ ፲፭ ከተዘረዘሩት ሰባቱ አጽዋማት አንዱ ሁኖ ከነሐሴ ፩–፲፭ የሚጾም ነው።
የባሕላዊው ጫዎታው ስያሜ የተወሰደው ልጃገረዶች ጠላልፈው በመጎንጎን በጀርባቸው አሥረው ከሚወዘውዙት አሸንዳ ተብሎ ከሚታወቅ ቀጤማ መሰል ሣር ነው። ይህ በላስታ አሸንድዬ ተብሎ የሚታወቀው የልጃገረዶች ባሕላዊ ጨወታ በዋግ ሻደይ፣ በራያ ቆቦ ሶለል በመባል ተቀራራቢነት ባላቸው ስያሜዎች ይጠራል። በሁሉም አካባቢዎች የሚታየው የአከባበር ሁኔታና ቀኑም ተመሳሳይ ነው። አብዘሀኛውን ጊዜ የአሸንድዬ ባሕላዊ ጨዋታ የሚከናወነው ከነሐሴ ፲፮-፳፩ ባሉት አምስት ቀናት ነው።
ለአሸንድየ በዓል መከበር መነሻ ምክንያት ናቸው የሚባሉ የቀደሙ የመጽሐፍ ቅዱስ አበው ታሪክ አልፎ አልፎም ቢሆን ይጠቀሳል። ከእነዚህም መካከል ከእሥራኤል መሳፍንት መካከል የዮፍታሔ ልጅ መታሰቢያ ልጆች ወይም ደናግል በየዓመቱ ሲያከብሩት የነበረውን በዓል እንደ አብነት በመውሰድ ነው የሚሉ አሉ። ሌሎች ደግሞ የአሸንዳን በዓል ከሊቀ ነቢያት ሙሴ መወለድ እና በውሃ ዳር ከቀጤማ ሥር መጣል ጋራ ያያይዙታል። በግብጽ አገር ሙሴ እንደተወለደ ማንኛውም ወንድ ዕብራዊ ሲወለድ እንዲገደል በግብጽ ዐዋጅ መውጣቱን ተከትሎ እናቱ እግዚአብሔር እንዳደረገ ያድርገው ብላ ከዐባይ ወንዝ ዳርቻ በቄጤማ ውስጥ አስቀምጣዋለች። በኋላ ግን የፈርዖን ልጅ ገላዋን ልትታጠብ ወደ ወንዝ (ዐባይ) ስትሄድ ደንገጡሯን ልካ አውጥታ በእናቱ ሞግዚትነት አሳድጋው እሥራኤልን ከተገዙበት የአራት መቶ ሠላሳ ዓመት ባርነት ነጻ እንዳወጣቸው ይታወቃል። ከዚህም በመነሳት ሙሴ የተጣለበትን ቄጤማ ስያሜ ወስዶ አሸንድዬ ተባለ ይላሉ። ልጃገረዶቹ በጨዋታቸው አበ ሙሴ፣ ወርቃ በሙሴ እያሉ ደጋግመው ማንሣታቸውን ለዚህ ማስረጃ አድርገው ያቀርባሉ።
እነዚህና መሰል ጉዳዮች የአሸንድዬ ባሕላዊ ጨወታ መነሻ ተደርገው ቢወሰዱም ዋናውና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው በዐል ግን ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰት ጋራ እየተያያዘ የመጣው የአከባበር ሥነ ሥርዓት ነው። በጒንጒን ታሥሮና ተጠላልፎ ለጨዋታ የሚታሠረው የአሸንድዬ ቅጠል መላእክት እመቤታችንን ክንፍ ለክንፍ ገጥመው ተያይዘው የማሳረጋቸው ምሳሌ ተደርጎ ይወሰዳል። ልጃገረዶቹ አሸንድዬ የሚባለውን የሣር ዐይነት ቅጠል በወገባቸው ጠምጥመው ተያይዘው ሲዘፍኑ መላእክት ድንግል ማርያምን ክንፍ ለክንፍ ገጥመው እያመሰገኑ ማሳረጋቸውን ያመለክታል።
ከዚህም ሌላ ሐመልማል ሙሴ በሲና ተራራ ከእሳት ጋር ተዋሕዶ ያየውን በቤተ ክርስቲያናችን በድንግል ማርያም የሚመሰለውን ቅጠል ይመሰላል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ የአሸንድዬ ቅጠል ሔዋን ዕፀ በለስን በልታ ራቁቷን በኾነች ጊዜ ያገለደመችውን ቅጠል ሲያስታውስ አረንጓዴ መኾኑ ደግሞ በሥዕለ ማርያም ላይ የምንመለከተውን የድንግል ማርያምን ሐምራዊ የልብስ ቀለም ያስታውሳል ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ልምላሜው የዐዲሱን ዓመት መምጣት ማብሰሪያም ተደርጎ ይወሰዳል።