ይህ የአማራ ትሥሥርር በቻይና ይፋዊ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ድረ-ገጽ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ልማድ፣ አርበኝነት፣ ቅርስ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችንም ጭምር ለአባላት በሚገባ እናሳውቃለን። የድረ-ገጹ ዋና አላማ የአማራን ታሪክ በሚገባ ለሁሉም በማስተማር ታሪካችንን ወደቀደመ ልዕልናው መመለስ ነው። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤ አንዲት ነጻ ሃገር ኢትዮጵያ -->

ጳውሎስ ኞኞ

ኅዳር 11 ቀን 1926 ዓ.ም ተወለዱ 

ምስል፦ ጳውሎስ ኞኞ 
ከ 89 ዓመት በፊት ልክ ኅዳር 11 ቀን 1926  አንጋፋው ጋዜጠኛ ፣ የታሪክ ተመራማሪና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ በቁልቢ ከተማ የተወለደበት ዕለት ነበር። ጳውሎስ ከግሪካዊው መርከበኛ ኞኞና ከኢትዮጵያዊቷ ወይዘሮ ትበልጫለሽ አንዳርጌ ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ ተወለደ። በልጅነቱ እጅግ መልከመልካም ስለነበረ እናቱ ያወጡለት የመጀመሪያ ስሙ “አማረ” የሚል ነበር። በኋላ የበኩር ስሙን በመጽሐፍ ቅዱሱ ጳውሎስ ተኩት። 

ጳውሎስ ትምህርቱን የተከታተለው እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነበር። ይህም የሆነው በጣሊያን ወረራ ምክንያት ነው። ብልህ አዕምሮና የፈጠራ ችሎታ የነበራቸው ሰው ስለነበሩ፤ በልጅነታችው የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ጣሊያንን ሲገድሉ ወይንም ሲማርኩ ሥዕል በመሣል ያሳዩ ነበር። ምንም እንኳን ትምህርታቸውን ከአራተኛ ክፍል መቀጠል ባይችሉም በተፈጥሮ የታደለውን የማንበብ፣ የመጠየቅና የመመራመር ተሰጥኦ በሚገባ በመጠቀም ራሱን በራሱ አስተምሮ በትምህርት ገፍተው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሱት በላይ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ስራ ማበርከት ችሏል። በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ለዓመታት መረጃ በመስጠት፣ በማስተማርና በማዝናናት ህዝብን በማንቃት በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፏል። የመማርን ትርጉም የምስክር ወረቀትና የደመወዝ ጭማሪ ከማግኘት ጋር ብቻ አያይዘው ለሚመለከቱ ሰዎች ጳውሎስ ህያው ወቃሽ ነው። ራስን በማብቃት ህልምን ማሳካት እንደሚቻል ከጳውሎስ ህይወት መማር ይቻላል።

ጳውሎስ የታሪክ ድርሳናትን በመመርመር በርካታ የታሪክ መጽሐፍትን ጽፏል። ልቦናውን በማንቃት የጻፋቸውን የፈጠራ ጽሁፎችንም ማሳተም ችሏል። የሴቶች አምባ፣ አጤ ምኒልክ ፣ አጤ ቴዎድሮስ ፣ አስደናቂ ታሪኮች ፣ የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት፣ አራዳው ታደሰ ፣ የኔዎቹ ገረዶች ፣ የጌታቸው ሚስቶች ፣ ምስቅልቅል፣ እንቆቅልሽ ፣ ከውጭ ሀገራት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች፣ አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች፣ እውቀትና ሌሎች መጽሐፍቶችን አሳትሞ ለአንባቢያን የቀረባቸው ናቸው። ለሕትመት ከበቁት ስራዎቹ በተጨማሪም የአጤ ዮሐንስ ታሪክ፣ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የአዲስ አበባ ታሪክ፣ የልጅ ኢያሱ ታሪክ፣ አዜብና ሰዎቹ የተሰኙ ያልታተሙት ስራዎች እንዳሉት ይነገራል።

ጳውሎስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በጸሐፊነት ለረጅም ዓመታት፤ በአዘጋጅነት ደግሞ ለጥቂት ወራት ያገለገለ ሲሆን፤“ደብዳቤዎቹ” እና “አንድ ጥያቄ አለኝ” የተሰኙ አምዶችን ያዘጋጅ ነበር። በርካቶች ጳውሎስን የሚያስታውሱት ትልቅ ተወዳጅነትንና ዝናን ባተረፈበት አንድ ጥያቄ አለኝ በሚለው የአዲስ ዘመን የጋዜጣ አምዱ ነው። ጳውሎስ ኞኞ ተወዳጅ በነበረው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የ አንድ ጥያቄ አለኝ አምድ የካቲት 1964 ዓ.ም እትም ላይ አንድ አንባቢ “እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በብዛት የሌለው ስም የቱ ነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ፣ “ኞኞ” ሲል መልሶ ነበር።

ጳውሎስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እየሰራ ፈለቀች ከተባለች ቆንጆ ጋር ፍቅር ሲይዘው አንድ ማህበራዊ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ግጥም ይጽፋል። የግጥሙ የመጀመሪያ ፊደሎች ከላይ ወደታች ሲነበቡ ፈለቀች ትወደኛለች እኔም እወዳታለሁ የሚል ዓረፍተ ነገር እንዲሰጡ በማድርግ ፍቅሩን በዘዴ እንደገለጸ ይነገራል። አጼ ኃይለሥላሴ በአንድ ወቅት “ዳንስ አገርን አይገነባም” በሚል ርዕስ የጻፈውን ጽሑፍ አንብበው ደስ ስለተሰኙ 300 ብር ሸልመውታል።


እግሩ ላይ የተከሰተው የአጥንት ካንሰር ህመም ቀስ በቀስ ጳውሎ ስን እንዳይንቀሳቀስ አደረገው። ወዳጆቹና አድናቂዎቹ ሳይነግሩት ገንዘብ አሰባስበው ፓስፖርት አውጥተው ወደ ጀርመን ተጉዞ እንዲታከም አደረጉት። የጀርመን ህክምናውን አጠናቅቆ ከተመለሰ በኋላ ህመሙ አገርሽቶበት አላላውስ ሲለው ሼክ ሙሃመድ አሊ አል-አሙዲ አሜሪካን አገር ወስደው አሳከሙት። ጤናውን ለመመለስ ብዙዎች የደከሙት ድካም ፍሬ ሳያፈራ ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም ይህቺን ምድር ተሰናበተ።

አለቃ ተገኝ ታምሩ ሩህ መጽሔት ቅጽ ቁጥር አራት ላይ የጳውሎስን ህልፈት አስመልክተው ተከታዩን ስንኝ ቋጥረውለታል።
በሺህ ዘጠኝ መቶ በሃያ ስድስት፣
በዘመነ ማርቆስ በጥቢ ወራት።
የምሥራቁ ኮከብ ያ ጳውሎስ ኞኞ፣
በኅዳር አሥራአንድ ተወለደ ሰኞ።
ብሩህ ከከብ ሆኖ ለሁሉም ሲያበራ፣
በጥበብ ጎዳና ሕዝቡን እየመራ፣
ታሪክ እየለየ ጣፋጭ ከመራራ፣
አንድ ቀን ሳይሰለች ለቁም ነገር ሥራ፣
የጳውሎስ አይነት ጸባየ ወላንሳ፣
ቀድሞም አልነበረ ኋላም አይነሳ፣
አጣነው በድንገት በግንቦት ሰላሳ፣
መሬት ምን ቸገራት ብትሰጠን መልሳ።
ውድ ጳውሎስ ኞኞ የአበሻው ፈረንጅ፣
የጽሑፍ የቃላት የታሪክ ባለእጅ፣
ሌት ቀን ረፍት የለው ሁሉን ሲያዘጋጅ፣
የስንፍና ጠላት የሥራ ወዳጅ፣
የድካሙን ፍሬ ትቶ ለልጅ ልጅ፣
በሥነ ተፈጥሮ በሥላሴ አዋጅ፣
በግንቦት ሰላሳ ፈሰሰ እንደጠጅ፣
ግን መሞቱ አይደለም ረፍቱ ነው እንጅ።

አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል


የአማራ ትስስር በቻይና

ኅዳር 11   2015 ዓ.ም 

ቻይና

 


የአማራ ትስስር በቻይና(ANiC)

የአማራ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ፣ ሃይማኖትና ባህል ያለው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት የሆነ፤ ሃገር የሰራ፣ ነጻነቱን ያስጠበቀ፤ የራሱ የሆነ ፊደል ያለው፤ የጥንታዊ ትምህርት ስርዓት ባለቤት የሆነ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ በሃገረ መንግስት ምስረታ ሃገርን ከወራሪ መጠበቅና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ታላቅ ገድል በመስራት እኛ ልጆቹ ቀና ብለን እንድንሄድ አድርጎናል።

Post a Comment

ቀዳሚ ገጽ ተከታይ ገጽ
hi