ታላቁ ሰው የሀገር ባለውለታ የታሪክ ጸሐፊ አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ
መስከረም 1 ቀን 1906 ሸዋ በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ በጊናገር ወረዳ፣ በአሳግርት ልዩ ስሙ አቆዳት በሚባል ስፍራ ተወለዱ። ወደ አዲስ አበባ መጥተው የመጀመሪያ ትምህርታቸውን በአማርኛና በግዕዝ ካጠናቀቁ በኋላ በቀድሞ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት የፈረንሳይኛ ትምህርት ተምረዋል። ለኢጣሊያ የወረራ ዘመን ሶስት ዓመታት በግዞት በሶማሊያ ቆይተዋል። ከዚያም ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ አገዛዝ ነፃ እንደወጣች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በአስተዳደርና በዲፕሎማሲ መስክ አገልግለዋል።
አቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ በኢትዮጵያ የንባብና የትምህርት ዓለም በስፋት የሚታወቁት ፅፈው ባዘጋጇቸው እጅግ ግዙፍ በሚባሉ መፃሕፍቶቻቸው ነው። በቀደመው ዘመን ላይ ለትምህርት ቤቶች የታሪክ መማሪያ በአምስት ቅፅ የታተሙት መፅሐፍቶቻቸው ነበር የሚያገለግሉት። የኢትዮጵያን ታሪክ ከማንም በበለጠ መልኩ የፃፉ ሰው ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ እርሳቸው የኢትዮጵያን ታሪክ ለባለታሪኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመፃፍ ይታወቃሉ። የእርሳቸው ዘመን ላይ የነበሩ የታሪክ ምሁራንም ሆኑ አሁን ያሉት ምሁራን በአብዛኛው የሚፅፉት በውጭ ሀገር ቋንቋ ነው። እርሳቸው ግን ለኢትዮጵያዊ ወገናቸው ውብ በሆነ የአፃፃፍ ስልታቸው ሲፅፉለት ነበር የኖሩት ።
ከታሪክ ጸሐፊነታቸው በተጨማሪ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ብዙ አገልግለዋል። ከጣሊያን ወረራ በኋላ ከ1934 ዓ.ም እስከ 1935 ዓ.ም በመዝገብ ቤት ሹምነት እና በሚኒስትር ጸሐፊነት ሰርተዋል። ከ1935-1966 ዓ.ም ደግሞ የምድር ባቡር ዋና ተቆጣጣሪ፣ በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዋና ፀሐፊ፣ የጡረታ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር፣ በረዳት ሚኒስትርነት ማዕረግ የብሔራዊ ቤተመዛግብት ወመዘክር ዋና ኃላፊ፣ በሚኒስትር ማዕረግ በእየሩሳሌም ቆንስል፣ በቤልግሬድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል። የአፄ ኃይለሥላሴ ስርዓት በኃይል ከተወገደ በኋላም በዘመነ ደርግ እስከ 1967 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የትምህርትና የባሕል ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸውን ታሪካቸው ያወሳል። ከዚያም በጡረታ ተገለሉ።
እኚሁ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ለንባብ ያበቋቸውን የኢትዮጵያን የታሪክ መፃሕፍት በአብዛኛው የፃፉት በመንግሥት ሥራ ላይ እያሉ የእረፍት ግዜያቸውን በመሰዋት ነው። ለሕትመት ከበቁላቸው አያሌ ሥራዎቻቸው መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው። እነዚህም፦
1. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣
2. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ልብነድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ፣
3. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ይኩኖ አምላክ እስከ አፄ ልብነድንግል፣
4. የኢትዮጵያ ታሪክ ከአክሱም ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ፣
5. የኢትዮጵያ ታሪክና ኑቢያ፣
6. ከጣኦት አምልኮ ወደ ክርስትና፣
7. ጥንታዊት ኢትዮጵያና ግብፅ
8. የሰው ጠባይና አብሮ የመኖር ዘዴ፣
9. የግራኝ አሕመድ ወረራ
10.አፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት
11.አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት እና ሌሎችም ያልታተሙ አያሌ ስራዎች አሏቸው።
ከላይ ከተዘረዘሩት መጽሐፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአክሱም ዛጉዌ እስከ ይኩኖ አምላክ የሚለውን ከዚህ አውርደው ማንበብ ይችላሉ።
እነዚህ ከላይ የሰፈሩት የታሪክ መፃሕፍት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ታላላቆቹ ቅርሶች እንደ አክሱም፣ ላሊበላና ጎንደር የሚታዩ እንደሆነ ጸሐፊያን ይናገራሉ። አሁን ያሉ ወጣት ጸሐፊያን የታሪክ መጽሐፍት እያሉ የሚያሳትሟቸው ስራዎቻቸው በአብዛኛው ከአቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ስራዎች የተገለበጡ ናቸው። የተኮረጁ ናቸው። የተሰረቁ ናቸው። ለአንዳንዶቹ ደግሞ የመነሻ ሃሳብ የሚሰጡ ናቸው። ተክለፃዲቅ መኩሪያ በኢትዮጵያ የታሪክ ፅሁፍ ውስጥ ዘላለማዊ ብርሃን ረጭተው ያለፉ ብርቅዬ ደራሲ ነበሩ። ይህንን ውለታቸውን ያስታወሰ ሌላ አካል ባለመኖሩ ላዕከ ተክለማርያም ሐምሌ 20 ቀን 1992 ዓ.ም ለተክለፃዲቅ መኩሪያ የሚከተለውን ቅኔ ያቀረቡት።
ያንድ ቤት ያስር ቤት የመቶ ቤት እያልን፣
የታሪኩን ሂሳብ ገና እያሰላሰልን፣
በሺ ቤት መቁጠሩን ሳንማርልዎ፣
አቶ ተክለፃድቅ ምነው መሔድዎ?
እንግሊዝ ፈረንሳይ ጣሊያኖች እረፉ፤ ሃሳብ አይግባችሁ፣
አይመጣም እንግዲህ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚጠይቃችሁ።
ያፄ ልብነ ድንግል የቦካን ተራራ፣
ያፄ ፋሲል ጎንደር የመቅደላ ጎራ፣
እንደ ተክለፃዲቅ ከሌለህ ወዳጂ፣
ማን ይፅፍልሃል ተረስተህ ቅር እንጂ።
ተክለፃዲቅ መኩሪያ የበቀለብሺ፣
ኩሪ አገሬ ቡልጋ ደብረ ፅላልሺ።
የተፈለፈለ የተሰራ ከአለት፣
እንደ ላሊበላ እንደ አክሱም ሐውልት፣
የታሪክ አምድ ነው ተክለፃዲቅ መኩሪያ፣
መናኸሪያ እሚሆን መነሻ መድረሻ።
ታሪክ ይመላለስ እንደ ለመደው፣
የማይመለሰው ተክለፃዲቅ ነው።
ከዚያ ከትልቁ ከሰማይ ቤት፣
የምትፅፈውን ታሪክ ለመስማት፣
ልሂድ ካንተ ጋራ አብሬ ልሙት፣
ተክለፃዲቅ መኩሪያ የታሪክ አባት።
የተክለፃዲቅ ነፍስ ምን ቸግሯት ቦታ፣
ቢሻት ከአብርሃም ጎን ከነ ይስሃቅ ተርታ፣
ቢሻት ከቴዎድሮስ ከዮሐንስ ጋራ፣
ቢሻት ከምንልክ ከተፈሪ ጋራ፣
ትኖራለች የትም እንደ ልቧ ሆና፣
እየፃፈች ታሪክ በጽድቅ ብራና።
ታሪክ አልማርም ባፍንጫዬ ይውጣ፣
ተክለፃድቅ መኩሪያ መምሕሬ ከታጣ።
ጥያቄ አትጠይቁኝ አታስቸግሩኝ፣
ተክለፃድቅ መኩሪያ ማነው አትበሉኝ፣
ጣይ ሞቆት ጣይ ሞቆት አገር ያወቀው፣
ተረት ተረት ሳይሆን ታሪክ ፃፊ ነው።
ተክለ ፃድቅ መኩሪያ
የታላቁን ሰው የህይወት ታሪክ የማያውቅ አይኖርም ቢሆንም አብዘሀኛ ደራሴዎችም ሆኑ እንደራሴወች የጥብብ ሰዎችም ይህን ታላቅ ደራሲ ሲያነሱት አልያም ሲያወሱት አይታይም። እንደዚህ አይንት የጥበብ ሰወችን ለትውልድ አይን እና ጆሮ የሆነን ትላንትን በዛሬ ታሪክን ለባለታሪኩ ያሰረከቡንን የታሪክ አባቶችን ማሰታወሰ ተገቢ ነው። በ1992 በላዕከ ተክለማርያም ለዚህ እንቁ ሰው ለተክለፃዲቅ መኩሪያ መታሰቢያ የተገጠመች ስንኝ ብቻ አቀረብኩላችሁ።
ምንጭ፦ ጆን አጋፔ (book for all page)
አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል
የአማራ ትስስር በቻይና
መስከረም 3 2015 ዓ.ም
ቻይና