ይህ የአማራ ትሥሥርር በቻይና ይፋዊ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ድረ-ገጽ የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ልማድ፣ አርበኝነት፣ ቅርስ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችንም ጭምር ለአባላት በሚገባ እናሳውቃለን። የድረ-ገጹ ዋና አላማ የአማራን ታሪክ በሚገባ ለሁሉም በማስተማር ታሪካችንን ወደቀደመ ልዕልናው መመለስ ነው። አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤ አንዲት ነጻ ሃገር ኢትዮጵያ -->

ዕረፍቱ ለዘርያዕቆብ

የዓፄ ዘርያዕቆብ ዕረፍት

 ወበዛቲ ዕለት በዓለ ዕረፍቱ ለዘርዓ ያዕቆብ ንጉሠ ነገሥት 

ትናንት ማለትም ጳጉሜ 3 ቀን የታላቁ ንጉሥ ዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ኅልፈተ ሕይወት 554ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ነው። ዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ከኢትዮጵያ ነገሥታት 265ኛው ነበሩ። ዘርአ ያዕቆብ በዘውድ ስማቸው ቆስጠንጥንዮስ ከአባታቸው ቀዳማዊ ዳዊት እና ከእናታቸው ንግሥት ክብረ እግዚእ በ1391 ዓ/ም ከአዋሽ ወንዝ አጠገብ ትገኝ በነበረው ትልቅ ተብላ በምትጠራ መንደር በቀድሞው ፈጠጋር ( Fetegar) ክፍለ ሐገር (በአሁኑ ኦሮሚያ ክልል) ተወለዱ። አባታቸው ቀዳማዊ ዳዊት ከ1375 እስከ 1404 ዓ/ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ።

የዓፄ ዘርአ ያዕቆብ የንግሥና ዘመን ከ1426 - 1468 ዓ/ም ነበር። ያረፉትም በዳጋ ደሴት ጣና ሃይቅ ነው። ከዓፄ ዘርአ ያዕቆብ አስቀድሞ ንጉሥ የነበረው ዓምደ ኢየሱስ ሲሆን ከዘርአ ያዕቆብ በመቀጠል ደግሞ በእደ ማርያም ነግሧል።

ምስል፡- ዓፄ ዘርያዕቆብ

የዘርዓ ያዕቆብ አባት ቀዳማዊ ዳዊት ባረፉ ጊዜ፣ እንደ ጥንቱ የኢትዮጵያ ባህልና ወግ መሰረት፣ ታላቅ ወንድማቸው የነበሩት ቀዳማዊ ቴዎድሮስ በ1414 ሲነግሡ ታናሽ ወንድማቸውን በግዞት ወደ አምባ ግሽን እንዲሄድ አደረጉ። ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብ ቆየት ብለው በጻፉት መጽሐፈ ብርሃን በተሰኘው ድርሰታቸው መሰረት እስከ ነገሡበት ሰኔ 20 ቀን 1434 ዓ/ም ድረስ በግዞት ግሸን ተራራ (አምባ ግሸን) ላይ ለ20 አመታት በእስር ኖረዋል። ሆኖም ግን በግዞት እያሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የደጋፊያቸው መጠን እየበዛ ሄደ። በነዚህ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከዓመት ወደ ዓመት እየተበላሸ ሄዶ በመጨረሻ ከአምባው ላይ ለሹመት ሲወርዱ አገሪቱ በእርስበርስ ሽኩቻ እየታመሰች፣ በሃይማኖት በኩልም መከፋፈል ተፈጥሮ የውጭ ኃይሎችም ከነገ ዛሬ አጠቁን እየተባለ የሚፈራበት ሁኔታ ገጠመው። የወደፊቱ ንጉሥ ብዙ እድሜውን ያሳለፈው ከሰው ተለይቶ አምባ ላይ ስለነበር፣ የዲፕሎማሲ ጥቅሙን አልተረዳውም ነበር። ይልቁኑ ፊት ለፊት የተጋረጡትን የሃገሪቱን ችግሮች በሚያስፈራ ድፍረት እና ምንም በማያወላዳ ጽናት ተጋፈጠው።

ዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ንጉሥ ከሆኑ በኋላ ንግሥት እሌኒን በ1434 ዓ/ም አገቡ፣ ከዚያም በ1436 ዓ/ም ዘውድ ጫኑ። ንግሥት እሌኒ የሀድያ ንጉሥ ልጅ ስትሆን በህጻንነቷ የእስልምና ዕምነት ተከታይ የነበረች ቢሆንም በጋብቻው ወቅት ክርስቲያን ሆናለች።


በ1442 ዓ/ም በሰንበት ላይ ተነስቶ የነበረውን የቤተክርስቲያን ክፍፍል ለማብረድ ቢችሉም እስከ 1450 ነገሩ ሲሰክን ቆይቱ በደብረ ምጥማቅ ጉባኤ (ተጉለት)፣ የግብጾቹ ጳጳሳት በተገኙበት ችግሩን ሊፈቱ ችለዋል። ሌላው በዘመናቸው የተከሰተው ሃይማኖታዊ ንቅናቄ የደቀ እስጢፋ ወገኖች እምነት ነው። እነዚህ እስጢፋኖስ የተባለ መነኩሴ ባስተማራቸው መሰረት ለመስቀል መስገድና ለሥዕለ አድኅኖ ለድንግል ማርያም መስገድ አይገባም የሚሉ ነበሩ። ተከራክረው ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብ አሸንፈዋል።


በ1445 እና ከዚያ በኋላ በተነሱ ጦርነቶች ላይ በመሳተፍ ሁሉን በድል በማጠናቀው ግዛታቸውን ያሁኒቷን ሶማልያን ሁሉ ያቅፍ ነበር። በ1456 ዓ.ም አጼ ዘርዓ ያዕቆብ በነበሩበት ቦታ ታላቅ ብርሃን ስለታየ የነበሩበትን ቦታ ደብረ ብርሃን በማለት የሃገሪቱ ዋና ከተማ አድርገው ቆርቁረዋል። እስከ እለት ህልፈታቸውም ደብረ ብርሃን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነበረች።


ዓጼ ዘርአ ያዕቆብ በጦር ውሏቸው ብቻ ሳይሆን የሚታወቁት ከ20 በላይ መጻሕፍትንም በመድረስና ለትውልድ በማቅረብ ጭምርም ነው። ከነዚህም መካከል ፤

1. መጽሐፈ ብርሀን 

2. መጽሐፈ ሚላድ 

3. መጽሐፈ ሥላሴ 

4. መጽሐፈ ባሕርይ 

5. ተዓቅቦ ምስጢር 

6. ጦማረ ትስብእት 

7. ስብሐተ ፍቁር 

8. ክሂዶተ ሰይጣን 

9. እግዚአብሔር ነግሠ 

10. ድርሳነ መላእክት 

11. ተአምረ ማርያም 

12. ዜና አይሁድ 

13. ጊዮርጊስ ወልደአሚድ 

14. ተአምረ ማርያም ወኢየሱስ 

15. ተአምረ ትስብኢት 

16. ልፉፈ ጽድቅ 

17. ትርጓሜ መላእክት 

18. ተአምረ ጊዮርጊስ 

19. ትርጓሜ ወንጌላት 

20. መልክዓ ማርያም

21. መስተብቁዕ ዘመስቀል ይገኙበታል። 

እነዚህ መጽሐፎች ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ሆነው በዘመናቸው የተነሱትን ለመስቀል ፤ ለድንግል ማርያምና ለሥዕለ አድኅኖ መስገድ የተገባ አይደለም ለሚሉት ደቀ እስጢፋ ለተባሉት ወገኖች እንደመልስ ሆነው የሚያገለግሉ ፤ ለትውልድ ማስተማሪያ የሚሆኑ ምሥጢር የሚገልፁ መጽሐፍት ናቸው።


(ዋቢ ምንጮች: 

Biography of Zara Yakub from Dictionary of African Christian Biography

The Chronicle of the Emperor Zara Yaqob, translated by Richard Pankhurst)

አዘጋጅ፦ የታሪክ ክፍል 


የአማራ ትስስር በቻይና

ጳጉሜ 4 2014 ዓ.ም 

ቻይና


የአማራ ትስስር በቻይና(ANiC)

የአማራ ሕዝብ የሚያኮራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ስነጽሑፍ፣ ሃይማኖትና ባህል ያለው፤ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት የሆነ፤ ሃገር የሰራ፣ ነጻነቱን ያስጠበቀ፤ የራሱ የሆነ ፊደል ያለው፤ የጥንታዊ ትምህርት ስርዓት ባለቤት የሆነ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ በሃገረ መንግስት ምስረታ ሃገርን ከወራሪ መጠበቅና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ታላቅ ገድል በመስራት እኛ ልጆቹ ቀና ብለን እንድንሄድ አድርጎናል።

Post a Comment

ቀዳሚ ገጽ ተከታይ ገጽ
hi